Pages

Wednesday, May 23, 2018

የብሔር ፖለቲካውን አደጋ እናስወግድ



 ከህሊና በላይ ፍርድን ማን ያቀናል?!
ከውቀት ሁሉ ልቆ
ከጥልቅ ስሜት ረቅቆ
በፍቅር የታነፀ
የሰላምን ብስራት
የፈጣሪን መልዕክት
ለሰው ማን ያደርሳል?!
በእውነት ከህሊና በላይ ምን አለ? ህሊና አይጨበጥም፣ አይዳሰስም፡፡ ስለመኖሩ ግን እናውቃለን - በልቦናችን ወይም በስሜታችን፡፡ ብቻ በሆነ መንገድ ህሊና እንዳለ እንረዳለን፡፡ ህሊና የፈጣሪ ፍርድ ወደኛ የሚደርስበት መንገድ ሳይሆን አይቀርም፡፡
እኔም በዛሬው ፅሁፌ፤ በህሊናዬ ለመመርመር የሞከርኩትን የአገራችን የብሔር ፖለቲካ ተዋስኦ፣ በህይወታችን ውስጥ እየተገለጠ ያለበትን ገፅታዎቹን አሳያለሁ፡፡ በፅሁፉ መጨረሻ ላይም አሁን ከገባንበት የብሔር ፖለቲካ አዙሪት ሊያስወጡን የሚችሉ የመፍትሄ አቅጣጫዎችን ለመጠቆም እሞክራለሁ፡፡
በእርግጥ የአንድ ግለሰብና የአንደ ተቋም ተሞክሮ እና ምልከታ፣ የአገራችንን ገፅታ ለማሳየት በቂ ሊሆን አይችልም፡፡ ነገር ግን በተለያየ አጋጣሚ ከወዳጅ፣ ዘመድ፣ ጎረቤትና ጓደኛ እንዲሁም ከመገናኛ ብዙሃን የምሰማቸው ተሞክሮዎች ተቀራራቢነት ከዚህ በታች የማቀርበው ትንታኔ በተወሰነ መልኩም ቢሆን የአገራችንን የብሔር ፖለቲካ ተግባራዊ ውጤት ያሳይ ይሆናል የሚል ግምትን አሳድሮብኛል፡፡
በመሆኑም ይህ ፅሁፍ የግል ተሞክሮን በመንተራስና በአጠቃላይ በአገራችን እየተከናወኑ ያሉ ሁነቶችን በመታዘብ የተዘጋጀ እንጂ የጥናት ፅሁፍ አለመሆኑን አንባቢው እንዲረዳልኝ እጠይቃለሁ፡፡


መንደርደሪያ
ቋንቋና ብሔርን መሰረት ያደረገው ፌደራሊዝም በአገራችን ከተተከለ ሶስት አስርት አመታትን ሊደፍን ምንም ያህል አልቀረውም፡፡ ለጊዜው ምን ዓይነት ፌደራሊዝም ብንከተል ይበጀን ነበር የሚለውን የፌደራል ስርዓት የሚያስገኛቸውን ጥቅሞች ለመቃኘት ብንሞክር በአገራችን ይህ ስርዓት ያመጣውን አዎንታዊ ለውጥ ለመታዘብ እንችላለን፡፡ በተለይም ደግሞ አስተዳደሩ ቀልጣፋ እንዲሆንና የአካባቢው ማህበረሰብ የባለቤትነት ስሜት እንዲያድርበት በማድረግ ረገድ ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወት ግልፅ ነው፡፡
እነዚህን ያልተማከለ የፌደራል ስርዓት ጥቅሞች ወደ አገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ስንመነዝራቸው፣ በአንዳንድ ዘርፎች ላይ የተመዘገቡ መልካም ውጤቶችን መጥቀስ እንችላለን፡፡ ለምሳሌ የትምህርትና የጤናው ዘርፍ ሽፋን መሻሻል በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የዚህ ስርዓት ለውጥ ውጤቶች ናቸው ብሎ መውሰድ ይቻላል። በውስጡ ብዙ አከራካሪ ጉዳዮችን የያዘ ቢሆንም በአገራችን ለተመዘገበው ተከታታይ የኢኮኖሚ እድገት፣ ያልተማከለ የፌደራል ስርዓት መከተላችን አንዱ አቅጣጫ ወይም ገፊ ምክንያት መሆኑን መገመት ከእውነታው አያርቀንም፡፡ እዚህ ላይ የፌደራል ስርዓቱ ትሩፋት ሊሆን የሚገባው ፍትሃዊ የሀብት ክፍፍል በተግባር ሲታይ፣ በተቃራኒው ኢ-ፍትሃዊነት ፅንፍ ላይ ያረፈ መሆኑ ግን የስርዓቱን የአተገባበር ችግር በግልፅ ያሳያል፡፡
በአጠቃላይ በአንዳንድ ወገኖች እንደሚገለፀው፣ የፌደራል ስርዓቱ የይስሙላ ነው የሚያስብሉ በርካታ ችግሮችን የተሸከመ ቢሆንም እንኳን በተወሰነ ደረጃ ከላይ የተጠቀሱትን አዎንታዊ ለውጦች እየተንገራገጨና እያዘገመም ቢሆን ለማስመዝገብ ችሏል፡፡ በአንጻሩ ግን ከፌደራል ሥርዓቱ ጋር ተጣብቆ፣አገሪቱን ከገደል አፋፍ ላይ ያቆማት ግልፅ አደጋ ፊት ለፊታችን ተጋርጧል፡፡ ይህም አደጋ የብሔር ፖለቲካችን ነው፡፡
የብሔር ፖለቲካ በስርዓቱ ውስጥ ግምባር ቀደም ስፍራ አግኝቶ በአገራችን ዘሩ የተተከለው ከፌደራል ስርዓቱ ጋር ነው ማለት ይቻላል፡፡ የእነ ዋለልኝ መኮንን ትውልድ “ኢትዮጵያ የብሔር ብሔረሰቦች እስር ቤት ናት” በሚል የጀመረው የአገራችን  የታሪክ፣ የባህልና የኢኮኖሚ ግጭቶች ገላጭ ነው ተብሎ የተወሰደ ትርክት፣ የሶሻሊስት ርዕዮተ ዓለም ተፅዕኖ፣ በጊዜ ሂደት ቅርፅ እያስያዘው መጥቶ፣ አሁን ለደረስንበት ምዕራፍ አብቅቶናል፡፡ በያንዳንዳች ህይወት ውስጥም ተፅዕኖውን እያሳረፈ ይገኛል፡፡ ዛሬ ላይ በንድፈ ሀሳብ ደረጃ ብቻ የምንሟገትበት ሁነት ሳይሆን እየተነፈስነው ያለው አየር ውስጥ የናኘ፣ የዕለት ተዕለት ኑሯችን አካል ሆኗል፡፡ ወደድንም ጠላንም በአሁኑ ወቅት የብሄር ፖለቲካ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ህይወታችን የሚቃኝበት ትልቁ ኃይል ነው፡፡
ይህንን የሚጠራጠር ካለ በእግር ኳስ ስታዲየሞቻችን ውስጥ ከጨዋታው መንፈስ ባሻገር፣ የደጋፊዎችን ቀልብ የገዛው መንፈስ ምንድን ነው ብሎ ይጠይቅ፡፡ የብሔር ፖለቲካው፣ ከፖለቲከኞች የመጫወቻ ካርድነት አልፎ በግለሰቦች ህይወት ላይ ተፅዕኖ የሚያሳርፍበት አቅም የለውም ብሎ የሚገምት የዋህ ካለ፣ ከተለያዩ ቦታዎች “አገርህ አይደለም” እየተባለ፣ ቤት ንብረቱ እየወደመ የሚፈናቀለውን ወገናችንን ጩኸት ለማዳመጥ ልብና ጆሮውን ይስጥ። የብሔር ፖለቲካ፣ በአገራችን ለዘመናት የኖረውን የብሔር ብሔረሰቦች ጭቆና ቀንበር ሰብሮ፣ “የተጨቆኑ ብሔሮችን” ነፃ ያወጣ የፖለቲካ ኃይል ነው የሚል ብዥታ ያለበት ቢኖር፣ ንፁሐን ወገኖቻችን “ለምን?” ብለው ስርዓቱን በመሞገታቸው ብቻ እስር ቤት የሚማቅቁት የብሔር ብሔረሰቦችን ጭቆና ማብቃት ለማብሰር ምስክር እንዲሆኑ ይሆን? የሚል ጥያቄ አቀርብለታለሁ፡፡
በሰው አገር ተሰዶ ከሰው በጋች የሆነ ኑሮውን የሚገፋው ወገናችንስ፣ በባይተዋርነት የህይወት አዙሪት ውስት የሚንከላወሰው፣ የብሔር ፖለቲካችን ትሩፋት በዝቶ ስለተትረፈረፈለት ይሆን? ሀገር ተረካቢ ትውልድን አንፀው ያወጣሉ የተባሉ ዩኒቨርሲቲዎችን የብሔር ግጭትን የሚፈለፍሉ፣ የጥላቻ ማምረቻ ፋብሪካዎቻችን አልሆኑም?  
በእርግጥ ለእነዚህ ሁሉ ጥያቄዎች አጭርና ቀላል ምላሽ ለመስጠት አንችል ይናል፡፡ ጥያቄዎቹ ግን ችግር ስለመኖሩ አመላካች መሆናቸውን የምንጠራጠር አይመስለኝም፡፡ “ችግር አለ” ከሚለው ከተነሳን እና “ችግሩ ሁላችንንም የሚነካ ነው” ወደሚለው ሃሳብ ከዘለቅን፣ በጉዳዩ ላይ ባለቤቶች ሆነናል ማለት ነው፡፡ ወደ መፍትሔውም አብረን መጓዝ እንችላን፡፡ አማራጭ የመፍትሄ አቅጣጫዎችን ፍተሻ ከመጀመራችን በፊት ግን ከብሔር ፖለቲካ ጋር የተገናኘ የግል ተሞክሮዬን ላካፍል፡፡
ተቋምን የሚያፈርስ ፖለቲካ ሀገርም ማፍረስ ይችላል
በአገራችን አንጋፋ ከሚባሉት በአንደኛው የፌደራል ሆስፒታል ውስጥ እሰራለሁ፡፡ ባለፉት ሁለት አመታት ብቻ በዚህ ሆስፒታል ውስጥ ያስተዋልኩትን የሁኔታዎች መገለባበጥ ለመረዳት ብዙ ማሰላሰል አስፈልጎኛል። በአንድ ወቅት ተቋሙ እጅግ በጣም ከፍ ካለ የተስፋ ማማ ላይ በመውጣት፣ ሀገራዊ የእይታ አድማሱ ሰፍቶ የታየበትና በተቃራኒው በአስገራሚ ፍጥነት ያ ሁሉ ተስፋና ተቋማዊ ሞራሉ ተንኮታኩቶ፣ የተቋሙ ሰራተኛ ወደ ተለያዩ ቡድኖች ተሸንሽኖ፣ በቁዘማ ውስጥ ተጠቅልሎ የተኛበትን ሂደት ስቃኘው፣ ክስተቱ ህልም ወይም ቅዠት እንጅ በአገራችን የሚገኝ የአንድ ትልቅ ተቋም እውነተኛ ታሪክ አልመስልህ ይለኛል፡፡
በዚህ ጉዳይ ላይ ከስራ ባልደረቦች ጋር ስጫወት፣ አንደኛው ወዳጄ፤ “አገራችንን በተቋማችን መስኮት በጨረፍታ አጮልቀን አይተን ታዘብናት” አለ፡፡ የዚህ ተቋም ታሪክ ያገራችን ታሪክ እንዳይሆን የዘወትር ፀሎቴ ነው፡፡ የሁኔታዎች መመሳሰል ግን “የፈሩት ይደርሳል፣ የጠሉት ይወርሳል” እንዲሉ ሌት ተቀን የሚያባንነኝ አስፈሪ ቅዠት ሆኖብኛል፡፡
የዚህን ተቋም የእድገት ጉዞ መጨናገፍ ሂደት በዝርዝር መተንተን የፅሁፌ ዋና አላማ ባለመሆኑ ትኩረቴን ተቋሙን በገጠሙት አንኳር ክስተቶች ላይ አድርጌ፣ እኝህም ክስተቶች ለተቋሙ ውድቀት መፍጠን ያበረከቱትን አስተዋፅኦ በመቃኘት ላይ አደርጋሁ፡፡ የተቋሙ ተሞክሮ ከአገራችን ወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታ አንፃር፣ ለአገር ግንባታ ሂደቱ ፖለቲካዊ አንድምታ ይኖረዋል የሚል ተስፋ አለኝ፡፡
እንደሚታወቀው የአንድ ሆስፒታል ዋና ዓላማ፣ የጤና እክል ያጋጠማቸውን ህሙማን ዘር፣ ቀለም፣ ሀይማኖት ሳይለይ አክሞ ማዳን ወይም እንዲያገግሙ መርዳትና በሽታን ለመከላከል የሚያስችል የግንዛቤ አቅምን ህብረተሰቡ እንዲያዳብር ማገዝ ነው፡፡ እኔ የምሰራበት ተቋምም ይህንን የተቀደሰ አላማ አንግቦ መስራት ከጀመረ በርካታ አስርት አመታትን ያስቆጠረ አንጋፋ ሆስፒታል ነበር፡፡ “ነበር” ያልሁት አሁን ካለበት ሁኔታ አንፃር፣ “ነው” ማለቱ ከብዶኝ ነው፡፡ የዚህ ተቋም ዘርፈ ብዙ በጎ ለውጦች ባለፉት አምስትና ስድስት አመታት ውስጥ እስከ 2009 ዓ.ም መዝለቅ ችለው ነበር፡፡
በተለይም ወደ ተቋሙ ለሚመጡ ተገልጋዮች የህክምና አገልግሎት ከመስጠት ባሻገር አገራዊ አድማስ ያላቸው የግንዛቤ ንቅናቄዎችን በመፍጠር፣ የተገልጋዩን ማህበረሰብ የጤና ንቃት ለማሳደግ ጥረት ይደረግ ነበር። ይህም ለረጅም ጊዜ የኖረውን የተቋሙን የገለልተኝነት ባህል መስበር የቻለ ክስተት ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡
… በዚህ ተቋማዊ የባህል ለውጥ ምክንያት ሆስፒታሉ በርካታ ትስስሮችን ከሌሎች ተቋማት እና ከተለያዩ የማህበረሰብ አካላት ጋር መፍጠር ቻለ፡፡ በፍቅርና በትብብር መንፈስ የተገነባው ተቋም ዜማ የተቀየረ መሰለ፡፡ ኧረ እንደውም አዲስ ዜማ በአገሪቱ ናኘ ማለት ይቻላል - እድሜ ትልቅ ልብ ለታደሉት የአገራችን ከያንያን፣ አርቲስቶች፣ ዘፋኞች እና የጥበብ ሰዎቻችን። እናም በ2009 ዓ.ም መግቢያ ላይ ተቋሙ የጀመረውን የጉዞ መዳረሻ ገፅታ ለማየት የሚያስችለው የዕድገት ማማ ላይ ወጣ፡፡ አብዛኛው የተቋሙ ሰራተኞችም የጋራ ራዕይ አንግበው፣ የቤተሰብ ያህል በፍቅር ተሰባሰቡ፡፡ ራዕያችን ይሳካል ወደሚል እምነትም ተሸጋገሩ፡፡ ሆስፒታሉ በተሰማራበት የህክምና ሙያ ዘርፍ ትልቅ ብሔራዊ የምርምር እና ስልጠና ማዕከል ለመገንባት የሚችልበት ጊዜ መቃረቡን አመላካች ጉዞ ላይ መሆኑ ታመነበት፡፡
… አሳዛኙ ክስተት እዚህ ላይ ነው ብቅ ያለው፡፡ በገለልተኝነትና በቅንነት ህዝብን ሲያገለግል የነበረው ተቋም፤ በፖለቲካ ጣልቃ ገብነት መናጥ ጀመረ። ጥቂት ቁጥር ያላቸው “የፖለቲካ ሰዎች” የብዙሀኑን ድምፅ ቀምተው በመጮኻቸው፤ ትልቅ ድምፅ እንዳላቸው ተደርገው ተወሰዱ፡፡ ምክንያቱም ፖለቲካው የፈጠረላቸውን ሰንሰለት ተጠቅመው ከዘረፉ የበላይ አመራሮች ጋር በተደጋጋሚ የመገናኘት ዕድል ያላቸው እነሱ ናቸው፡፡ የግል ጥቅም ፍላጎቶቻቸውን ለማሟላት፣ በየእለቱ የሚፈጥሯቸው የብሔር መድሎ ተረቶች ሰሚ ጆሮ አገኙ፡፡
በተለይም የብሔር ጩኸት በቀላሉ የብዙ ሰዎችን ደም የሚያሞቅ ነዳጅ በመሆኑ የተወሰኑ ሰዎችን ንፁህ ህሊና መበረዝ ቻሉ፡፡ በምክንያት ማሰብና በቅንነት ማገልገል በአጭር ጊዜ ውስጥ ግብዓተ መሬታቸው ተፈፀመ፡፡ “ግርግር ለሌባ ያመቻል” እንዲሉ “ሁሉ ጉዳይ በብሔር ዓይን ካልታየ” እንዲሉ “ሁሉ ጉዳይ በብሔር ዓይን ካልታየ” የሚሉ አዋቂ ነን ባዮች አድራጊ ፈጣሪ ሆነው ብቅ አሉ፡፡ ዘርና ቀለም የማይለየውን የጤና ጉዳይ በብሄር ፖለቲካ መነፅር ካልፈተሽነው የሚል ሀሳብ መግነን ጀመረ። በቅንነት የሚሰሩ ሰዎችን በዘር ከረጢት ውስጥ እያስገቡ ማሸማቀቅ የእለት ተእለት ተግባር ሆነ፡፡ በሰው ልጆች ሁሉ የጤና እክል ላይ የዘመተውን ተቋም፣ እራሱን የዘር በሽታ ተጠቂ አድረጉት፡፡
ዛሬ በሬውን ሸጦ፣ ልጆቹን ጦም አሳድሮ፣ ወንዝ አቋርጦ ህክምና ለማግኘት ለሚመጣው ወገናችን የምንሰጠው ምላሽ፤ “በአንተ ስም የምንዋጋውን ጦርነት ስላልጨረስን የጤና አገልግሎት ልንሰጥህ አንችልም” የሚል ይመስላል፡፡ እውነት ነው፤ ቅን አሳቢ ባለሙያዎቻችን፣ ከተቋማችን እየፈለሱ ወደ ሌሎች ተቋማት መንጎድ ጀምረዋል፡፡ ምናልባትም ተመሳሳይ ሁኔታ በየሄዱበት የማይገጥማቸው ከሆነ፣ ውሳኔያቸው ትክክል ነው ብዬ አስባለሁ፡፡
በመጨረሻም አንባቢ፤ “አንተስ የነሱን ፈለግ ተከትለህ አትፈልስም ወይ?” የሚል ጥያቄ ሊያቀርብልኝ ይችላል። አንደኛው መልሴ፤“የትም ብሔድ ብዙ ለውጥ ይኖረዋል ብዬ ስላልገመትሁ ያለሁበትን ተቋም በድሮው መውደዴ እየወደድሁት ዛሬን አሳልፈዋለሁ። ነገንም በናፍቆትና በተስፋ እጠብቃለሁ” የሚል ይሆናል፡፡ የታላቁ ባለቅኔ የደበበ ሰይፉ ግጥም ስሜቴን በጥሩ ሁኔታ ይገልፅልኛል፡-
እኔና ወንድሞቼ ሁላችን ሁላችን
ከባዶ አቆማዳ ነው ሚዛቅ ፍቅራችን
ሁለተኛው ምላሽ ደግሞ “ሁኔታው ከባድ ቅሬታን ቢያሳድርብኝም በግለሰቦች ላይ ቅሬታን ወይም ቂምን አለመያዜ ነው ተቋሙን እንዳልለቅ ያደረገኝ” የሚል ይሆናል፡፡ የዝሆኖች ጠብ የሚረግጡትን ሳር ያወድማል እንደሚባለው፣ በዚህ ግርግር በመጨረሻ በዘላቂነት ተጎጂ የሚሆነው ከተቋሙ፣ የጤና አገልግሎት የሚጠብቀው ማህበረሰብ ቢሆንም በዘርና ብሔር ክፍፍል ተመርዘው የሚፈራገጡት ግለሰቦችም ቢሆኑ የዚሁ የዘር ፖለቲካ ተጠቂዎች ናቸው፡፡ ሊታዘንላቸው እንጅ ቂም ሊያዝባቸው ይገባል የሚል እምነት የለኝም። እናም ሁሉም የማልጠላቸው ወንድሞች ናቸው፡፡ ዛሬ ላይ የሚያሳዝኑኝ፣ ነገ ላይ ደግሞ ምናልባትም ወደ ንፁህ የህሊና ሚዛናቸው ቢመለሱ፣ የምኮራባቸው ወገኖች ናቸው፡፡ ዋናው ቁም ነገር የምንተነፍሰው የተመረዘ አየር ቢቀየር፣ ለሁላችንም የሚበጀን መሆኑን መረዳቱ ላይ ትኩረት ማድረግ ነው፡፡
የመፍትሄ አቅጣጫ
መቸም ፖለቲካ የሰው ልጅ የህይወት መከራን ለመቀነስ የተበጀ ነው ብለን ካመንን፣ “ሰው ሰው” የሚሸት እንዲሆን እንጠብቃለን፡፡ ፖለቲከኞቻችንም በአገር ፍቅር ስሜት ተነሳስተው ርዕዮተ ዓለማቸውን የሚቀርፁ ከሆነ፣ የፖለቲካው መንፈስ በጥላቻ ሳይሆን በሰው ልጅ ፍቅር ላይ የተተከለ ይሆናል፡፡ ምክንያቱም አገር መውደድ ማለት ሰውን መውደድ እንጅ ሌላ ሊሆን አይችልም፡፡ ተወዳጁ ደራሲ  በዓሉ ግርማ፤በተከታዮቹ ስንኞች  በውብ ቋንቋ ገልፆታል፡፡
ከጎራው ዘልቄ እስኪ ልነጋገር
ካለሰው ቢወዱት ምን ያደርጋል አገር
የኔ ውብ ከተማ
ህንፃ መች ሆነና የድንጋይ ክምር
የኔ ውብ ከተማ
መንገድ መች ሆነና የድንጋይ አጥር
የኔ ውብ ከተማ የኔ ውብ አገር
የሰው ልጅ ልብ ነው
የሌለው ዳርቻ የሌለው ድንበር
የምንመኘው አገር በበዓሉ ግርማ ግጥም ላይ የተሳለው የሰውን ልጅ የሚያከብርና የሚያፈቅር መንፈስ የሰፈነበትን ዓይነት ከሆነ በብሔር ፖለቲካው ጉዞ መዳረሻችን የምናገኘው ስለመሆኑ ከባድ ጥርጣሬ አለኝ፡፡ ከመፈቃቀር ይልቅ ወደ መፎካከር፣ መጨቃጨቅ መጠላላትና መጠፋፋት የሚወስደን መንገድ ላይ የምንገኝ ይመስለኛል፡፡
በእስካሁኑ ጉዟችን ልምድ መሰረትም መመስከር የምንችለው ይህንኑ ነው። ችግሩ የመንገዱ ሳይሆን የተጓዞቹ ወይንም የጉዞ መሪዎቹ ነው የሚል ክርክር ሊነሳ ይችላል፡፡ በዚሁ መንገድ ላይ ሌሎች መሪዎች ቢተኩ፣ የተለየ ውጤት ይመጣል ብለው የሚያምኑ ሰዎች አሉ፡፡ በእርግጥም እነዚህ መሪዎች የያዝነው መንገድ እንደማያዋጣን ተረድተው፣ አዲስ መንገድ የሚቀይሱ መሪዎች ከሆኑ ትክክል ነው፡፡ ዞሮ ዞሮ ግን መንገዱ መቀየር አለበት፡፡
አንዳንድ ጊዜ ቅርፅ ይዘትን ይወስናል፡፡ የወይን ብርጭቆ እየተመለከተ የወተት አምሮቱ የሚቀሰቀስበት ሰው የለም፡፡ የብሔር ፖለቲካም ከፍቅር ይልቅ የጥላቻና የግጭት ቋት መሆኑን አይተናል፡፡ እሳት በውሃ እንጂ በእሳት እንደማይጠፋ እናውቃለን፡፡ የብሔር ጭቆናን በብሔር ፖለቲካ ለማጥፋት መሞከር፣ እሳትን በእሳት ለማጥፋት እንደ መሞከር ይቆጠራል፡፡
ፖለቲካ በባህሪው ፉክክርና ውድድር የሚጋብዝ መድረክ ነው፡፡ የፖለቲካ ቡድኖች የሚያደርጉት ውድድር ወይም ፉክክር በአንድ አገር ውስጥ የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎችን ወክለው ሲሆን የእነሱ መሸናነፍ ትርጉሙ የህዝብ መሸናነፍ ይሆናል፡፡ ተወካይ ቡድኖች ደግሞ የዘር፣ የቀለም፣ የፆታና የሀይማኖት ልዩነትን መሰረት አድርገው የተዋቀሩ ሲሆን ፉክክሩ ወደ ጥላቻና መጠፋፋት ለማደግ ጊዜ አይወስድበትም። የዚህን ውጤት በእግር ኳሳችንም ላይ እየታዘብነው መሆኑን ልብ እንበል፡፡ እዚህ ላይ አሜሪካዊው የፖለቲካ ሳይንቲስት ሳሙኤል ሀንቲንግተን፤ የሰው ልጆች ለደም ትስስር ያላቸውን ጠንካራ ስሜት የገለጹበትን መንገድ መመርመር፣ የእኛን ሁኔታም ለመፈተሽ ይረዳናል፡፡ አባባሉ የሚከተለው ነው፡-
“What ultimately counts for people is not political ideology or economic interest. Faith and family, blood and belief, are what people identify with and what they will fight and die for.”
በግርድፉ ሲተረጎም፤ “ከፖለቲካዊ ርዕዮተ ዓለም ወይም ኢኮኖሚያዊ ፍላጎቶች ይልቅ በደም ትስስርና በእምነት ላይ የተመሰረቱ ግንኙነቶች ሰዎችን እስከ ሞት ድረስ በፈቃደኝነት እንዲሰው የሚያደርጉ ኃይሎች ናቸው” የሚል ነው፡፡
በአጠቃላይ ከላይ ለማብራራት በተሞከረው ፅንሰ ሀሳብ መሰረት፤ ብሔርን ምርኩዝ ያደረገው የፌደራል ስርዓታችን ተግዳሮቶች የሚከተሉት ናቸው፡-
1ኛ. በብሔሮች መካል የሚነሱ ግጭቶች መበራከት እና አገሪቱን ወደ ቀውስ መምራት
2ኛ. የተጠያቂነት መመናመን እና የሙስና መንሰራፋት
3ኛ. በገለልተኛ ተቋማት ላይ የሚደርሱ ድንበር የለሽ ጣልቃ ገብነቶች
4ኛ. መጨረሻ የሌለው የማንነት ጥያቄ
5ኛ. የብሔሮችን ባህላዊና ማህበራዊ ዕሴቶች ለፖለቲካ መጠቀሚያነት በማዋል የእሴቶቹን ዋጋ ማቀጨጭ
በመጨረሻም የችግሩን አቅጣጫ በማስተዋል መፍትሄ ለመስጠት የምንገደድበት ወቅት ላይ መድረሳችን እሙን ነው፡፡ የብሔር ፖለቲካው ሌላው ቀርቶ በዋነኝነት ይፈታዋል ተብሎ የታለመውን የብሔር ብሔረሰቦችን የነፃነት፣ የፍትህና የእኩልነት ችግሮች በተቃራኒው ውል ወደሌለው ውስብስብ ግጭት እንደመራው አይተናል። በመሆኑም የመፍትሄያችን ማጠንጠኛ፣ የብሔር ፖለቲካውን አቅጣጫ በመተለም ላይ ትኩረት ማድረግ ያለበት ይመስለኛል። ብዙ የአፍሪካ አገራት፣ ቅኝ ገዢዎች በብሔርና በጎሳ በማቧደን ያደርሱባቸው የነበሩ ቀውሶችን  ምክንያት በማድረግ፣ ከነጻነት በኋላ የፖለቲካ ፓርቲ በብሄር እንዳይቋቋም በህግ እስከ ማገድ ደርሰዋል፡፡
በተቃራኒው በእኛ አገር ባለፉት ሶስት አስርት አመታት ውስጥ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ መንገድ ብሔር ተኮር ፓርቲዎች በፖለቲካው መድረክ ላይ ሲበረታቱና ህብረ ብሔራዊ ፓርቲዎች ደግሞ በተለያዩ ጫናዎች አማካኝነት እንዲፈራርሱ ሲደረጉ ታዝበናል። ነገር ግን እንደ ሌሎች የአፍሪካ አገሮች ብሔር ተኮር ፓርቲዎችን በህግ እስከማገድ ባይደርስ እንኳን ቢያንስ ህብረ ብሔራዊ ፓርቲዎች ፍትሃዊ የውድድር ዕድል የሚያገኙበትን ሁኔታ በማቻቸት የአገራችን የፖለቲካ አቅጣጫ፣ ከብሔርና ከጎሳ ተኮር ፖለቲካ እንዲላቀቅ ማስቻል ተገቢ ይመስለኛል፡፡
ይልቁንም በደርግ ጊዜ ተጀምሮ የነበረውን የኢትዮጵያ ብሔረሰቦች ጥናት ኢንስቲትዩት እንደገና በማደስ፣ የብሔር ብሔረሰቦችን የነፃነት፣ የፍትህና የእኩልነት ጥያዌዎች ምላሽ መስጠት የሚያስችል የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት የሌለበት ተቋማዊ አካሄድ መቀየስ ይበጃል፡፡ የፌደራል አወቃቀሩንና ሕገ መንግስቱንም እንደገና መፈተሽ አስፈላጊ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ከሁሉም በላይ ግን ሁሉንም አካታች የሆኑ ክፍት የውይይት መድረኮች እንዲበራከቱ በማድረግ፣ የተለያዩ የፖለቲካ አመለካከት ያላቸው ልሂቃን ሀሳባቸውን መሰንዘር እንዲችሉ መበረታታት አለበት፡፡ ይህ ብሔራዊ የእርቅ መድረኮችንም ያካትታል፡፡ ሁሉም የሚሆነው ግን የዲሞክራሲ መብቶች በማይሸራረፉበት ጣሪያ ስር ነው፡፡ 

No comments:

Post a Comment