Pages

Tuesday, May 29, 2018

ሱስ ያደበዘዛቸው የሕይወት መስመሮች


በአፍሪካ ትልቁ ገበያ እንደሆነ በሚነገርለት በመርካቶ እንኳንስ ነጋዴው ተላልኮ የሚኖረው ምስኪን እንኳ ገንዘብ አይቸግረውም፡፡ ሌላው ቢቀር የዕለት ጉርስ ጉዳይ አያሳስበውም፡፡ የወላጆቹን የንግድ ሥራ ድርጅት ገና በልጅነቱ ለተቀላቀለው ለካሳሁን ኪሮስ ዓይነቱ ደግሞ ገንዘብ ቁም ነገሩ አይሆንም፡፡ ‹‹ብዙ ገንዘብ አገኝ ነበር፡፡ ማግኘቴን እንጂ ቆጥሬም አላውቅም፤›› ይላል ገና በ12 ዓመቱ የመርካቶን ፈጣን የንግድ እንቅስቃሴ የተቀላቀለበትን ደጉን ጊዜ ሲያስታውስ፡፡
     በንግዱም ብቻ ሳይሆን በትምህርቱም ብርቱ የነበረው ኪሮስ የስምንተኛ ክፍል ብሔራዊ የመልቀቂያ ፈተና ላይ 95 ነጥብ አስመዝግቦ ነበር ወደ ዘጠነኛ ክፍል የተዘዋወረው፡፡ በዚህ ግን ሊቀጥል አልቻለም፡፡ እንደ ልቡ የሚያገኘው ገንዘብ ከጉርምስና ጋር ተደምሮ ማንኛውንም ነገር እንዲሞክር በሕይወቱ አላስፈላጊ ቁማር እንዲጫወት መንገድ ከፈተለት፡፡ ከጓደኞቹ ጋር ሆኖ የማይወጣው ተራራ የማይወርደው ቁልቁለት አልነበረም፡፡ አደገኛ የሚባሉ ሱሶችን በተለይም መጠጥና ጫትን ይሞክርም ጀመረ፡፡

     እንደ ቀልድ የተጀመረው ነገር ገንዘብ ለማይቸግረው ኪሮስ እንደ ጊዜ ማሳለፊያ ሆነው፡፡ በዕድሜ ከሚበልጠው ከአንድ ግለሰብ ጋር የፈጠረው ጉድኝት ደግሞ ሁሉንም ነገሮች አጠናክሮ እንዲቀጥል ምክንያት ሆነለት፡፡ ይሞክራቸው የነበሩ የመጠጥ ዓይነቶችም እየጨመሩ ሄዱ፡፡ የሚያውቁት ሰዎች እንዳያዩት ከሰፈሩ ራቅ ብለው የሚገኙ መጠጥ ቤቶችን ማሳደድን ሥራው አደረገ፡፡
     ገና በልጅነቱ ገንዘብ እንደ ልቡ ለሆነለት ኪሮስ፣ ማሪዋና መጀመርም ከባድ አልነበረም፡፡ የሚገዛበት ጊዜ ባይኖረው እንኳ ጩልሌ ጓደኞቹ ገዝተው ይጠብቁታል፡፡ ነገሮች ከቁጥጥሩ ውጪ የሆኑበት ግን የሐበሻ አረቄ ከቀመሰ በኋላ ነበር፡፡ እንደ ቀልድ የጀመራቸው መጠጥና የተከለከሉ ዕፆችን መጠቀም ወደ ሱስነት ደረጃ ሲሸጋገሩ ሳያውቀው ሕይወቱም ይመሰቃቀል ጀመረ፡፡ ትምህርቱን ከ11ኛ ክፍል አቋርጦ አረፈው፡፡ በሁኔታው ክፉኛ ይቆጩ የነበሩ ወላጅ አባቱ ብዙም ሳይቆዩ ሞት ቀደመቻቸውና እንደ አባት ሆኖ ቤተሰቡን የማስተዳደር ኃላፊነት ገና በልጅነቱ ሱሰኛ በሆነው ኪሮስ ጫንቃ ላይ አረፈ፡፡
    በአጋጣሚው ቢያዝንም ገንዘብ ያለተቆጪ እንደፈለገ እንዲመዝ ዕድል ግን ፈጠረለት፡፡ አልፎ ተርፎ ሱቁ ወደ መክሰር ሲል ያልቻለበትን ንግድ ለእናቱ አስረክቦ ውሎውን በጫትና አረቄ ቤቶች ዙርያ አደረገ፡፡ ቀልጣፋ ለሆነው ኪሮስ ገንዘብ ማግኘት ቀላል ነበረና ግብሩን ለማድረስ ገንዘብ አጥሮት አያውቅም፡፡ ሲያስፈልገው አፈ ቀላጤ ደላላ፣ ሲያስፈልገው ደግሞ እሳት የላሰ ግንበኛ ሆኖ ብዙም ሳይደክም በቀን እስከ ሺሕ ብር ማግኘት ይችላል፡፡ ኪሮስ በየቀኑ የሚያገኘው ገንዘብ አንድን ቤተሰብ ከድህነት የማውጣት አቅም ቢኖረውም እሱን ግን በተቃራኒው ድህነት ውስጥ ይከተው፣ ከቀን ወደ ቀንም የጤናው ሁኔታ እየሰፋ እንዲሄድ ያደርገው ጀመር፡፡
     ሚስት አግብቶ ሁለት ልጆች የወለደ ቢሆንም ለቤተሰቡ ኃላፊነት እንዳለበት አይሰማውም ነበር፡፡ በሚያገኘው ገንዘብ እንደ ሕይወቱ የሚወዳትን የኮሶ አረቄ ይጨልጣል፡፡ ባጃጅ የሚላትን በትንሿ የራኒ ጁስ ጠርሙስ የሚቀዳለትን የኮሶ አረቄ ‹‹ከነ አረፋዋ ተሰፍራ ሳያት፣ እንኳን ሳልጨልጣት ሳያትም እረካለሁ፤›› ይላል ፊቱ በፈገግታ እንደተሞላ፡፡ ኪሮስ በሚያዘወትራቸው መሸታ ቤቶች ባጃጅ የአምስት መለኪያ አረቄ ልኬት ነው፡፡ ‹‹የተላላሰ አረቄ አልወድም፡፡ በመለኪያ እየለኩ ሲቀዱ በመሃል የሚንጠባጠብ የሚባክን ይኖራል፡፡ ስለዚህ ነው ባጃጅን የምመርጠው፤›› ሲል የምትባክን የአረቄ ጠብታ እንዳትኖር ምን ያህል እንደሚጠነቀቅ ይናገራል፡፡ አንዴ ጭልጥ የሚያደርጋት ባጃጅ ግን ጥሙን አትቆርጥለትም፡፡ በቀን ሠርቶ ያገኘው ከኪሱ እስኪያልቅ፣ መሸታ ቤቶቹ እስኪዘጉ ድረስ ባጃጁን ይጋተራታል፡፡
     በዚህ ሁኔታው ከባለቤቱ ጋር አብረው መኖር ስላልቻሉ ለመለያየት በቁ፡፡ ከቤተሰቡ ፍቅር ይልቅ የማይደራደርበት የአረቄ ናፍቆቱ ብርቱ ነበረና የትዳሩን መፍረስ እንደ ውድቀት ሳይሆን እንደ ነፃነት ነበር የቆጠረው፡፡ ቀን ከሌት ያለ ገደብ በየመሸታ ቤቱ እየዞረ በነፃነት አረቄውን ያንቃርር ገባ፡፡ ‹‹እኔ እና እንቅልፍ አንተዋወቅም፡፡ መጠጣት የምጀምረው ገና ሳይነጋ ነው፡፡ ውድቅት 9 ሰዓት ላይ የሚከፈቱ አረቄ ቤቶች አሉ፡፡ እነሱ ጋ ሂጄ እየጠጣሁ እቆይና ከዚያ ቤት ቀይሬ ሌላ ቦታ እየጠጣሁ አነጋለሁ፤›› የሚለው ኪሮስ እየጠጡ በስካር መንፈስ ውስጥ ሆኖ ሥራ ለመግባት ይቸገር ስለነበር እንደ ደላላ ሆኖ ከሚሠራበት ጫማ ቤት ለቆ ተባራሪ ሥራዎችን ለመሥራት እንደተገደደ ይናገራል፡፡
     እንዲያም ሆኖ በየቀኑ ሠርቶ የሚያገኘው ገንዘብ ጥቂት የሚባል አይደለም፡፡ ይሁንና ያገኘውን ሁሉ አመድ አድርጎ ማደር ልማዱ ላደረገው ኪሮስ በቀን የሚያገኛትን ብር ከሁለት ጠርሙስ አረቄ በዘለለ ትርጉም የለውም፡፡ እንደ ነፍሱ የሚወዳት የኮሶ አረቄ ቀስ በቀስ ሱስ መሆኗ ቀርቶ የሞት ሽረት ጉዳይ፣ የሞት መድኃኒት ያህል ታስፈልገው ጀመር፡፡ መዝናኛነቷ ቀርቶ የአየር ያህል የምታስፈልገው ውድ ማዕድን ሆነችበት፡፡
     ያለ አረቄ መንቀሳቀስም ሆነ መሥራት ተሳነው፡፡ አረቄ ካላገኘ እጁ ክፉኛ ይንቀጠቀጣል፣ መራመድ አይችልም ሰውነቱ ይንዘፈዘፋል፡፡ እስከ እኩለ ሌሊት በሚጠጣው ካቲካላ የናወዘ አዕምሮው ያመጣለትን እየለፈለፈ፣ መሬት አልቆነጥጥ የሚሉት እግሮቹ እንደ ቄጤማ እየተልፈሰፈሱ ወደ ማደሪያው ሲሄድ በኪሱ የሚያስቀረው ቀን ሠርቶ ከሚያገኘው ገንዘብ ላይ 15 ብር ብቻ ነው፡፡
     ይህቺ 15 ብር ቁርሱን የሚበላባት፣ በታክሲ ወደዛ ወደዚህ የሚልባት ሳትሆን ከከባድ ስቃይ የምትገላግለውን አንድ ባጃጅ አረቄ የሚገዛባት ነች፡፡ ከአንድ ሺሕ ብር በላይ ዋጋ እንዳላት የሚሰማውን 15 ብር በምንም ዓይነት ወድቃ እንዳትጠፋ፣ ማጅራት መቺ እንዳይወስድበት በውስጥ ሱሪው ውስጥ ደብቆ ሌሎች አረቄ ቤቶች እስኪከፈቱ ይጠባበቃል፡፡ እንቅልፍ የሚወስደው በስካር መንፈስ ከአንዱ ጥግ ወድቆ መነሳት ሲያቅተው ራሱን ሲስት ነው፡፡
     ውድቅት ዘጠኝ ሰዓት ላይ ፓርኪንሰንስ በሽታ እንዳለበት እየተንዘፈዘፈ ከአንዱ አረቄ ቤት መግቢያ ላይ ሲደርስ በድጋፍ እንደቆመ አስተናጋጇ አምስት መለኪያ አረቄውን በራኒ ጠርሙስ ትሞላለታለች፡፡ ባሪያዋ ያደረገችውን አረቄ አንስቶ ለመጠጣት የሚንቀጠቀጡ እጆቹ የዳገት ያህል ይከብዳቸዋል፡፡ ስለዚህም አስተናጋጇ በነካ እጇ ከአፍ እስከ ገደፉ በአረቄ የተሞላውን ጠርሙስ ወደ ኪሮስ አፍ ትልከዋለች፡፡ አንዴ ጭልጥ ሲያደርገው ነፍሱ እንደመመለስ ይላል፣ የሚንቀጠቀጡ እጆቹም በመጠኑ መረጋጋት ይጀምራሉ፡፡ ከዚያም እንደ ማንኛውም የቤቱ ደንበኛ አንድ ጥግ ይዞ አረቄውን ይኮመኩም ይገባል፡፡
     የሚከፍለውን ቢያጣ እንኳ በአረቄ አምሮት አንደበቱ የሚያያዝበትን፣ እግሮቹ የሚዝለፈለፉና የሚንቀጠቀጡትን የኪሮስን እጆች አይተው አይጨክኑበትም፡፡ እንደሱ ያለ የከተማውን አረቄ ቤቶች ያላመደ ደንበኛ ላይ የሚጨክን ልብም የላቸው፡፡ ሠርቶ እንደሚከፍል አስምለው አይዞህ ብለው ይግቱታል፡፡ ገንዘቡን ሳይሰስት የሚጋብዛቸው ጓደኞቹም ብድራቸውን ከመመለስ ወደ ኋላ አይሉም፡፡
ሱሱ ያደበዘዘውን የኪሮስን የሕይወት መስመር ዳር ቆሞ ላጤነው ቅዠት ይምሰል እንጂ ለኪሮስ ግድም አይሰጠውም፡፡ እንዴት ባደርግ ይሻለኛል ብሎ የሚጨነቀው አሳሳቢ ደረጃ ላይ ለደረሰው የጤናው ሁኔታ ሳይሆን ከአረቄ ቤት ወጥቶ ወደ ማደሪያው በመሄድ የሚያጠፋውን ጊዜ በሆነ ተአምር ስለመቀነስ ነው፡፡
     ከቤት ወደ አረቄ ቤት በመመላለስ የሚባክነውን ጊዜ ለመቀነስ ከአንድ ደንበኛው ጋር ተነጋግሮ አንድ መላ ዘየዱ፡፡ ደንበኛው አረቄ የሚሸጡበትን ክፍል እንደ ፎቅ በቆጥ ለሁለት በመክፈል ኪሮስና መሰሎቹ ሌሊት ሌሊት ቆጡ ላይ ወጥተው እንዲያድሩ ተስማሙ፡፡ የኒኩለር ፊዚክስ ያህል የከበደውን የሚጠጣበትን ሰዓት የማራዘም ጥያቄ በዚህ መልሶ በቀን አሥር ብር እየከፈለ እዚያው እየጠጣ እዚያው ማደር ጀመረ፡፡ አንዳንዴም ቆጡ ላይ መውጣት እየከበደው ወንበር ሥር እንደ ወደቀ ይተኛል፡፡ መሠረቱ ከደህና ቤተሰብ ለሆነው ኪሮስ የሰብዕናው ዝቅ ማለት ግድም አይሰጠው፡፡ ምንም ቢመጣ ክብሩን አስጥላ ያልከሰከሰችውን አረቄ ለመሸሽ ድፍረቱ የለውም፡፡
     ይኼንን የተመለከቱ ቤተሰቦቹ ግን አለመታከት እንዳይሆኑ ሆኖ የጠፋውን ማንነቱን አግኝቶ አደብ እንዲገዛ የማይፈነቅሉት ድንጋይ አልነበረም፡፡ ለአረቄ ያለውን ክብርና የጠለቀ ፍቅር ቢመለከቱ ምናልባት ክፉ መንፈስ ተጠናውቶት ይሆን ብለው ሽንቁሩ ሚካኤል ቤት ተከራይተውለት ፀበል እንዲሞክር አደረጉት፡፡ ነገር ግን በአቅራቢያው በድብቅ የሚሸጠው አረቄም ሆነ ማድ ቤት ተደብቀው የሚያጨሱት ሲጋራ ልፋታቸውን ከንቱ አደረገው፡፡ ዛሬ አቶ ኪሮስ በመካከለኛ ዕድሜ ላይ የሚገኙ ጎልማሳ ናቸው፡፡
 ለ26 ዓመታት በሱስ ውስጥ የኖሩት የ45 ዓመቱ አቶ ኪሮስ ሱስ በቃኝ ያሉት ሐኪሙ ‹‹በጣም አዝናለሁ መሞትህ ነው፤›› ካላቸው በኋላ ነበር፡፡
     በአዲስ ሕይወት የሱስ ተጠቂዎች ማገገሚያ ማዕከል ገብተው ወደ ራሳቸው ከተመለሱ ሁለት ወራት ተቆጥረዋል፡፡ ባለፈው ሳምንት ሪፖርተር ሲያነጋግራቸው ሕክምናቸውን ጨርሰው ለመውጣት የቀሯቸው ሁለት ቀናት ብቻ ነበሩ፡፡ በአንድ ግቢ ውስጥ ሲኖሩ እንደ ቤተሰብ ለሚያቀርቧቸው ሌሎች አገጋሚዎች አርአያ መሆን ችለዋል፡፡ ወደ ማገገሚያው ከገባ ገና አንድ ወር ከሆነው ዓይን አፋሩ ሚናስ (ስሙ ተቀይሯል) በቆይታቸው በበቂ ተዋውቀዋል፡፡ ስላለፈበት ሕይወት ነግሯቸዋል፣ የእሳቸውንም ጠንቅቆ ያውቃል፡፡
     ተወልዶ ያደገው ወግ አጥባቂ በሆነ ማኅበረሰብ ውስጥ በሰሜን ኢትዮጵያ ቢሆንም፣ ሚናስን የለየለት ሱሰኛ ከመሆን ግን አላገደውም፡፡ ስለ ራሱ ለመናገር ብዙም ድፍረቱ የለውም፡፡ የሚያኮራ ታሪክ እንደሌው ስለሚያውቅ መደበቅን ይምረጥ እንጂ እንደማይታዘበው እርግጠኛ የሚሆንበትን ሰው ሲያገኝ ከፊልም የማይተናነስ ታሪኩን እያስታወሰ የልቡን ያወራል፡፡
     ሚናስ እንደ ነውር የሚታየውን መጠጥና ጫት ከዕድሜ እኩዮቹ ጋር ሆኖ የጀመረው ገና በልጅነት ዕድሜው ነበር፡፡ በአንድ አጋጣሚ ወደ አዲስ አበባ የመጡ ጓደኞቹ ማሪዋና ይዘው ይመለሳሉ፡፡ ከተለመደው ወጣ ብለው ሊሞክሩ ያሰቡትን ዕፅ ከጥቅሉ ፈተው አሳዩት፡፡ ከመጠጥና ጫት ውጪ ሌላ ለማያውቀው ሚናስ ማሪዋናውን መሞከር አስፈርቶት እንደነበር ያስታውሳል፡፡
     ነገር ግን ከጓደኞቹ ላለመለየት በወረቀት ጠቅልለው ሰጡትና እንደ ሲጋራ ወደ ውስጥ ሳበው፡፡ ልዩ በሆነ የደስታ ስሜት ውስጥ ሆኖ ሲፈነጥዝ ሲፍለቀለቅ ትዝ ይለዋል፡፡ በአንድ ጊዜ ሚያጦዛቸው ማሪዋና እንደ አልኮል ወይም እንደ ጫት ዋጋው ብዙም ኪስ የማይጎዳ ነበረና ወደደው፡፡ በየአጋጣሚው አዲስ አበባ በተመላለሱ ቁጥርም ለብዙ ጊዜ የሚሆናቸውን በርከት አድርገው ይገዙ ስለነበር ማሪዋና አጥተው አይቸገሩም ነበር፡፡ ነገሩ የተበላሸው ጓደኞቹ ኑሯቸውን አዲስ አበባ ሲያደርጉ ማሪዋናው ሲቋረጥበት ነው፡፡
     በወቅቱ ሚናስ ከሰው ለመግባባት፣ ደስተኛ ለመሆን ሌሎችም ነገሮችን ሁሉ ለማድረግ ማሪዋና ላይ ጥገኛ መሆን የጀመረበት ነበርና እውነታውን መቀበል ተሳነው፡፡ በማሪዋና ናፍቆት ከቤተሰቦቹ መግባባት፣ ትምህርቱን መከታተል አቃተው፡፡ ራሱን እንደመሳት አድርጎት ልብሱን አውልቆ በአደባባይ እስከ መታየት ደርሶ ሁሉ ነበር፡፡ የነበረው አማራጭም ማሪዋና ማግኘት እንደ ልቡ እንዲችል ትምህርቱን ከዘጠነኛ ክፍል አቋርጦ አዲስ አበባ የሚኖሩ አክስቱ ዘንድ መምጣት ነበር፡፡
     በመጣ በአራት ቀናት ውስጥ ስልክ ደዋውሎ ማሪዋና ከሚያቀባብሉ ደላሎች ጋር ሲገናኝ ሰፊው የአዲስ አበባ ገፅታ አላደናገረውም፡፡ የሚፈልገውን ያውቃልና የጠሩት ቦታ እየሄደ፣ የቀጠራቸው ሰፈር እየተገናኙ ኪሎ ሜትሮችን አቋርጦ የመጣለትን ማሪዋና እንደ ልቡ ማግኘት ቻለ፡፡ ‹‹እንደመጣሁ ደወልኩላቸውና ያለሁበት መተው ይዘውኝ ወደ አራት ኪሎ ሄዱ፡፡ እኔ በመጣሁበት ወቅት ብዙ ‹ዊድ› ቤቶች ነበሩ፡፡ እንትና ቤት እንሂድ፣ እንትና ጋ ይሻላል እየተባባልን ነበር የምንሄደው፤›› የሚለው ሚናስ እዚህ እንደመጣ አራት ኪሎ ወዳለው በድብቅ ማሪዋና የሚጨስበት ቤት ሲገባ ከብዙ መሰሎቹ ጋር እንደተገናኘ፣ አብዛኞቹም የኮሌጅ ተማሪዎች እንደነበሩና አጠቃላይ ሁኔታው ጥሩ ስሜት አሳድሮበት እንደነበር ያስታውሳል፡፡
     የማሪዋና ሱስ በተጠናወተው በመጀመርያዎቹ ጊዜያት የሚያስፈልገውን ለመግዛት ገንዘብ አይቸግረውም ነበር፡፡ ለአንድ ዙር የሚጠቀሙት ማሪዋናም በክብሪት ቀፎ እየተለካ በአንድ ብር ብቻ ይሸጥ ስለነበር እንዲያውም ነገሮች ቀላል ነበሩ፡፡ በዚያ ላይ ማሪዋና ሲገዙ መታየት የማይፈልጉ ተማሪዎችና የቤት ልጆች ሚናስን ሲልኩት የሚያስቡለት ገንዘብም ግብሩን ለማድረስ የሚያንሰው አይደለም፡፡ ባይከፍሉት እንኳ ከገዛላቸው ላይ ለራሱ ቀንሶ ያስቀር ስለነበር ማሪዋና አጥቶ አያውቅም ማለት ይቻላል፡፡
     ‹‹በፊት እንኳን ቀጥታ ከሻጮቹ ገዝተን መጠቀም እንችል ነበር፡፡ አሁን ግን ቀጥታ ሻጮቹን አይደለም የምናገኘው ደላሎችን ነው፡፡ ዋጋውም በጣም ጨምሯል፡፡ ነገር ግን አሁንም በጭፈራ ቤቶች መግቢያ ላይ የሚሸጡ ጀብሎዎች አሉ፤›› ይላል ጠዋት ከእንቅልፉ ሲነቃ ጀምሮ ማሪዋና የሚያስፈልገው ሚናስ፡፡ ስለ ዓለም ጥሩ ስሜት የሚያድርበት ማሪዋና ሲስብ ብቻ ነው፡፡ ጨዋታ ሲያምረው፣ በራስ መተማመኑ ሲቀንስ ብቻ ለሁሉም ነገር መልሱ ማሪዋና ነው፡፡
     ውሎና አዳሩ ማሪዋና ማጨስ በሚችልባቸው አካባቢዎች የተወሰነ ነው፡፡ ጓደኝነት የሚጀምረውም በተመሳሳይ ሱስ ከተለከፉ መሰሎቹ ካልሆነ ችግር ነው፡፡ ‹‹ተነጋግሮ ለመግባባት ለመተዋወቅም አስቸጋሪ ይሆናል፤›› ሲል በገሀዱ ዓለምና ማሪዋና በሚፈጥረው ሌላው ዓለም ውስጥ ሆኖ በአንድ ቋንቋ መግባባት እንደማይቻል ከልምዱ ይናገራል፡፡ ስለዚህም ነው በዙሪያው ካሉት ውጪ ከሌሎች ጋር መጎዳኘትን የሚጠላው፡፡ በፍቅር የተመኘችው ካለች አብራው ጊዜ ለማሳለፍ ስትል ለኩሶ የሚሰጣትን ማሪዋና መሳብ ግዴታዋ ነው፡፡ ለመገናኘት የሚቀጣጠሩትም መቃሚያ ቤት፣ ጭፈራ ቤት አልያም ማሪዋናና ሌሎች መጠጦች በሚሸጥባቸው ሚስጥራዊ ቤቶች ነው፡፡
     ‹‹እኔን ብለው የመጡ ብዙ ሴቶችን ሱሰኛ አድርጌያለሁ፡፡ እንደኔ ከፍ ካላለች አብሮ ለማሳለፍ በጣም አስቸጋሪ ነው፤›› የሚለው ሚናስ ከማገገሚያው ሲወጣ ከበፊት ጓደኞቹ ጋር ተመልሶ ከገጠመ ልፋቱ ከንቱ እንደሚሆን ሥጋት እንዳለው ይናገራል፡፡ እንደ እሱ ደፍረው ማሪዋና ከሕይወታቸው ለማውጣት ጥረት የማያደርጉ ጓደኞቹን ነገር ሲያነሳ ያዝናል፡፡ አንደኛው ጓደኛው ትዳር ይዞ ልጆች ያፈራ ቢሆንም፣ እስካሁን ግን ሱሱን መግታት አልተቻለውም፡፡ ለነገሩ የትዳር አጋሩም ተመሳሳይ ችግር ስላለባት ተው ብሎ የሚያስገድደውም የለም፡፡ ‹‹እንዲያውም ልጆቻቸው እየረበሹ ሲያስቸግሯቸው ማሪዋና ያጨሱባቸዋል፤›› በማለት ጥንዶቹ እንኳንስ ከሱስ ራሳቸውን መታደግ ልጆቻቸውንም ወደዚህ መንገድ እየመሯቸው እንደሚገኙ ይናገራል፡፡
     በማገገሚያው በካቲካላ ልክፍት፣ በማሪዋና አባዜ ሲናውዙ የዕድሜያቸውን ግማሽ ካሳለፉ እንደነ ኪሮስና ሚናስ ካሉት በተለየ የሕመም ማስታገሻ መድኃኒት ሱስ አድሮባቸው የሚሰቃዩ ዜጎችም ተኝተው እንዲያገግሙ ይደረጋሉ፡፡
     ማገገሚያውን ከቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ጋር በአጋርነት ያቋቋሙት ሲስተር ይርገዱ ሀብቱ እንደሚሉት፣ የጫት የአልኮልና የሀሽሽ ሱስ ተገዠ የሚሆኑ ወጣቶች ቁጥራቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ይገኛል፡፡ በሕመም ማስታገሻ መድኃኒቶች ሱስ የሚያዙ ዜጎች ጉዳይም አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ ትውልዱን አደጋ ላይ እየጣሉት ከሚገኙ ማስታገሻ መድኃኒት ሱሶች ዋነኛውም ፔቴዲን ነው፡፡
     ፔቴዲን እንደ ማንኛውም የሕመም ማስታገሻ በዋዛ የሚታዘዝ መድኃኒት አይደለም፡፡ ማዘዣውን ከማግኘት ህመሙን ችሎ ማሳለፍ ሁሉ ይቀላል፡፡ ይህ ከባድ ማስታገሻ የሚታዘዘው በከባድ የቀዶ ሕክምና ወቅት የሚሰማን አሰቃቂ የሕመም ስሜት ለማስታገስ አልያም የአጥንት ስብራት አደጋ የደረሰባቸውን ታካሚዎች ስቃይ ለመቀነስ ነው፡፡ ከአቅም በላይ በሆነ አጋጣሚ ካልተገደዱ በስተቀር ከአንድ መርፌ በላይ መስጠት አይመከርም፡፡ ለአንድ ታካሚ ፔቴዲንን ከሁለት ጊዜ በላይ መስጠት ታካሚውን ከድጡ ወደ ማጡ እንደ መገፍተር ነው፡፡
     ‹‹እኔ 35 ዓመታት በሕክምና ሙያ አገልግያለሁ፡፡ በእነዚህ ዓመታት ውስጥ አንድ ጊዜ ብቻ ነው ሁለት ፔቴዲን ሰጥቼ የማውቀው፡፡ አሁን ግን ለቀላል ቀዶ ሕክምናና ለጨጓራ ሕመም ሳይቀር ፔቴዲን ይታዘዛል፡፡ አደገኛነቱን እያወቁም በቸልተኛነት እስከ አራት ፔቴዲን ለታካሚው የሚሰጡ ባለሙያዎች አሉ፡፡ ታካሚው የትናንቱን መድኃኒት ስጡኝ ብሎ ስለጠየቀ የሚሰጡ ባለሙያዎችም ያጋጥማሉ፤›› የሚሉት ሲስተር ይርገዱ ታማሚዎች በሕክምና ሒደት ሳያውቁት ለከባዱ የፔቴዲን ሱስ ተገዥ እየሆኑ እንደሚገኙ፣ ትልልቅ የሕክምና ባለሙያዎች፣ ነርሶች፣ ፋርማሲስቶች ደግሞ መድኃኒቱን በቅርበት ስለሚያገኙ በከፍተኛ ሁኔታ ለፔቴዲን ሱስ እየተጋለጡ እንደሚገኙ ሲናገሩ በቁጭት ነው፡፡ መድኃኒቱን ከጥቁር ገበያ ላይ በብዛት የሚያገኙ ሲሆን፣ ያለ ማዘዣ ፔቴዲንን እንደዋዛ ለጠየቃቸው ሁሉ የሚሸጡ ፋርማሲዎችም አሉ፡፡
     መድኃኒቱ ከአደገኛነቱ ባሻገር ዋጋውም ከባድ ነው፡፡ አንዱ መርፌ እስከ 70 ብር ድረስ ይሸጣል፡፡ ይሁንና ዋጋው ሱሰኞቹን ገዝተው ከመጠቀም የሚያግዳቸው አልሆነም፡፡ አንዱን እስከ 70 ብር እየገዙ በቀን 20 መርፌ ድረስ በደምስራቸው የሚወስዱ አሉ፡፡ አሁንም አሁንም አምጡ የሚላቸውን የጋለ ፍላጎት ለማርካት ጊዜ ስለማይበቃቸው ከትምህርትና ከሥራ ገበታቸው ቀርተው የፔቴዲን ያለህ ሲሉ ሲባዝኑ ይውላሉ፡፡ ሱሱ በጣም ከባድ በመሆኑ ለደህንነታቸው ሳይሰጉ አንድ መርፌ ተቀባብለው በቡድን እስከ መጠቀም ይደርሳሉ፡፡
     ‹‹በዚህ ሱስ ውስጥ የሚገኙ ሰዎች አብዝተው መድኃኒቱን በተጠቀሙ ቁጥር ሰውነታቸው ይቦጨቃል፡፡ በጣም ስለሚቆስሉ አክሞ ማዳንም ከባድ ነው፡፡ ሁለመናቸው ነው የሚታመመው፤›› የሚሉት ሲስተር ይርገዱ ከፔቴዲን ሱስ ማገገም በጣም ከባድ እንደሆነ ከልምዳቸው ይናራሉ፡፡ በአንድ ጊዜ ማቆም የማይታሰብ በመሆኑ እንዲያቆሙ የሚደረገው ቀስ በቀስ ነው፡፡ እንዲያም ሆኖ በየሰዓቱ አምጡ የሚላቸውን ስሜት ተቋቁሞ ማለፍ ትልቅ ፈተና ነው፡፡ የሕክምና ሒደቱን መቋቋም ሲከብዳቸው ከማገገሚያው ካልወጣን ብለው ያስቸግራሉ፣ እንደ ሕፃን ሊያለቅሱም ይችላሉ፡፡ የሚፈልጉትን ሲያጡ ደግሞ ተመልሰው ወደ ከባድ የድብርት ስሜት ውስጥ ይገባሉ፡፡
     ማገገሚያ ማዕከሉ ሥራ በጀመረ አራት ወራት ጊዜ ውስጥ አምስት የፔቴዲን ሱሰኞች ታክመውበታል፡፡ ሲስተር ይርገዱ በዚህ ሙያ በቆዩባቸው ዓመታት ውስጥ ደግሞ በርካታ የፔቴዲን ሱሰኞችን አስተናግደዋል፡፡ ከማይረሳቸው አጋጣሚ መካከልም በአንድ የፋርማሲ ባለሙያ ላይ የደረሰውን አስታውሰዋል፡፡
     ግለሰቡ የራሱ ፋርማሲ ያለው የተከበረ ባለሙያ ቢሆንም፣ ከፔቴዲን ሱስ ራሱን ሊከላከል ግን አልቻለም፡፡ በፋርማሲው የሚገኘውን መድኃኒት ለሕሙማን በማድረስ ፈንታ የራሱን ሱስ ማስታገሻ አደረገውና አረፈው፡፡ ፍላጎቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ በመጣ ቁጥር በቀን የሚወስደው የመርፌ ብዛትም በዚያው መጠን እያደገ፣ ፋርማሲውም ከገቢው በላይ ወጪው እያመዘነ ይሄድና ለኪሳራ ይዳረጋል፡፡ ይህም የማንቂያ ደወል ሆኖ ከሱሱ እንዲፋታ ምክንያት አልሆነውም፡፡ ይብስ ብሎም ፋርማሲውን ጨምሮ ያለውን አጠቃላይ ንብረት ሸጦ ባገኘው ገንዘብ ሱሱን ሲያስታግስበት ይከርምና ባዶ እጁን ይቀራል፡፡
     በስተመጨረሻም ወደ ሕክምና መስጫ ተቋም እንዲገባ ተደረገ፡፡ እንዲህ ካለው አደገኛ ሱስ በቀላሉ መገላገል የማይታሰብ ነው፡፡ በየሰዓቱ ካልተወጉ ውጪ ነፍስ ግቢ ነፍስ የሚላቸው ነገር እስከ 15 ቀናት ድረስ ሊቆይ ይችላል፡፡ በእነዚህ የጭንቅ ቀናት ውስጥ ተሳክቶላቸው ወደ ማገገሙ የሚጠጉ ዕድለኞች ናቸው፡፡ ሰዓታቸው ደርሶ መድኃኒቱን የሚተካ ሌላ ነገር እስኪሰጣቸው አልያም ራሱ ፔቴዲን እስኪሰጣቸው ምጥ እንደያዛት ነፍሰ ጡር ይንቆራጠጣሉ፣ ነፍሱ አልወጣ ብላ እንደተቸገረ ሟች ያጣጥራሉ፡፡
     ‹‹አክስቱ ፔቴዲን እንድትገዛ ተልካ ከወጣች ሰዓት ጀምሮ በር በሩን ሲያይ ቆይቶ መጣች፡፡ ነገር ግን መድኃኒቱ አልተገኘም ነበርና አምርሮ አለቀሰ፡፡ አረጋግቼውና መክሬው ሰዓቴ ደርሶ ወጣሁ፡፡ እሱ ግን ያለ ፔቴዲን አንድ ቀን ማደር አልሆን ብሎት በሚተኛበት አንሶላ ራሱን ሰቅሎ ሞተ፤›› ሲሉ በፔቴዲን ሱስ ተይዞ እንዳይሆኑ ሆኖ የሞተውን የፋርማሲ ባለሙያን ታሪክ ሲያስታውሱ፡፡ ሒደቶቹን ታግሰው ማለፍ የሚችሉም ቢሆኑ አገግመው ከወጡ በኋላ አገርሽቶባቸው ሁለት ሦስት ጊዜ የሚመላለሱ እንዳሉም ይናገራሉ፡፡

No comments:

Post a Comment