Pages

Wednesday, May 23, 2018

ግንቦት 20 ሲመጣ የሚታወሱኝ ሁነቶች


ግንቦት 20፣ 1983 ዓ.ም አዲስ አበባ (1)




 
ግንቦት 20 ቀን ሲመጣ ሁልጊዜም የሚታወሱኝ እነዚያ በልጅነት ዘመኔ ያየኋቸው ፀጉራቸውን አንጨብርረው አፋቸው የሚያስተጋባ የኢህአዴግ ታጋዮች ናቸው። በዚያን ወቅት አያቴ “አየሁ ብያ” ትለኝና “አቤት” ስላት “ከደርግና ከኢህአዴግ ማን ይሻላል?” ብላ ትጠይቀኛለች፤ እኔ ሁለቱንም ምን እንደሆነ ለይቼ ስለማላውቅ ከአፌ የመጣልኝን እናገራለሁ፤ ታዲያ ይህን ጥያቄ በተለያየ ቀን ነው ደጋግማ የምትጠይቀኝ።





አሁን ድረስ የሚገርመኝ “ኢህአዴግ” ብዬ ስመልስላት እሷ በመናደድ “ደግሞ እኒህ ገደቢስ እግረ ነጮች፣ ቅማላቸውን ይቅመሉ እንጂ” ትለኛለች። “ደርግ” ብዬ ስመልስላት ደግሞ ደስ እያለት ለሌላ ሰው የእኔ ልጅ ከደርግና ከኢህአዴግ ማን ይሻላል ብዬ ብጠይቀው “ደርግ” ብሎ መለሰልኝ፤ ልጅ እኮ የልቡን ነው የሚናገረው እያለች የወሬ ማድመቂያ ታደርገኛለች። ያው ቀደምቶቻችን አንድን ዘመን የሚመለከቱት ዘመኑን ተከትሎ በሚመጣ እርዚቅ አልያም ችግር ነው። የኢህአዴግ መምጣት የቀደመ ኑሯቸውን ስላናጋባቸው በበጎ አይመለከቱትም ነበር።





ግንቦት 20፣ 1983 ዓ.ም አዲስ አበባ (2)
እኒህ ታጋዮች ወደ ከተማችን የመጡት አሁን ትልቅ ሆኜ ጊዜውን ሳሰላው በ1981 መጨረሻ ገደማ ላይ ነው (ሰሜኑ የወሎ ክፍል ላይ በይፋ መግባት የጀመሩት አዲስአበባ ከመግባታቸው ዓመት ከስድስት ወር ቀደም ብሎ ነው)። በእኛ ከተማ ጦርነት አልተካሄደም ነገር ግን እኒህ ጨብራሬ ወታደር የማይመስሉ ታጋዮች ሆን ብለው ከተማው ውስጥ ተሰግስገው በመመሸጋቸው እነሱን ለመደብደብ መስከረም 23 1982 ላይ ከተማችን በጀት ተደበደበች፤ ይህ ከመሆኑ በፊት ቀድመው የሚያውቁት ሴረኛ ታጋዮች በሰልፍ ሆነው ከተማውን ለቀው በመውጣት ከከተማ ውጭ ወደሚገኝ ጫካ መሽገው ነበር።
ሴራ ማለት እንዲህ ነው፤ ልክ የሀውዜን ዓይነት ነው። በዚህ ድብደባ ወደ 20 ገደማ የከተማችን ሰዎች ሞተዋል። ጀቶቹ ቦንብ ሊጥሉ ሲመጡ አልጋ ያድን ይመስል እናቴ ትንሹንና ጡት የሚጠባውን ወንድሜን እሷ ታቅፋ እኔን በአልጋ ውስጥ ደብቃኝ ነበር። የጀቱ ድብደባ ሲያበቃ አያቴ ሌላ ሰፈር ነበረችና “ልጆቼ ተርፈው ይሆን” እያለች ወደ እኛ እየሮጠች ስትመጣ፤ እናቴ ደግሞ እኔና ትንሽ ወንድሜን ይዛ “ወይኔ እናቴ” እያለች ስትሄድ መካከል መንገድ ላይ ሲገናኙ ይታወሰኛል። ግንቦት 20 እንደ እንቆቆ የሚመረው ፍሬው ብቻ ሳይሆን ታጋዮቹንም ያስታውሰናል።





ግንቦት 20፣ 1983 ዓ.ም አዲስ አበባ (3)
ኢህአዴግ በጦርነት ጉዳት የደረሰባቸውን ከተሞችና አካባቢዎች ከሌላው የተለየ ቅድሚያ በመስጠት አለማለሁ ቢልም የኔዋ ከተማ ተብዬ ግን እንኳን ቅድሚያ ልማት ልታገኝ መደበኛውም የተጓደደበት ናት። በእርግጥ ይኼ ዕቅድ በራሱ ትግራይ ብቻ ነው የተደበደበችው በማለት፤ ትግራይን የበለጠ ተጠቃሚ ለማድረግ ታሳቢ በማድረግ ይመስለኛል፤ እንዲያ ባይሆን ኖሮ የኔዋም ከተማ የተለየ ቅድሚያ ባገኘች። በእውነቱ ካየነው ግን ከትግራይ ከተሞች በላይ የደርግ የመጨረሻ ዱላ ያረፈባቸው የዋግ ሰቆጣን ጨምሮ አብዛኞቹ የሰሜን ወሎ ከተሞች ናቸው ቆቦ፣ መርሳ፣ ወልዲያ፣ ሙጃ ወዘተ። ከትግራይ ያላነሰ እኛም በጦርነት ተደቁሰናል ብሎ ልክ እንደ ትግራይ የልዩ ልማት ተጠቃሚወች እንሁን ብሎ ጥያቄ ያቀረበ የብአዴን ሰው መኖሩን እጠራጠራለሁ።
ስለ ደርግ መንግስት
በሌ/ኮሎኔል መንግስቱ ዘመን ብወለድም፤ ስለ እሳቸው መንግስት ዘመን የማውቀው በመጽሀፍ ነው። ከኢህአፓው አመራር ከክፍሉ ታደሰ “ያ ትውልድ ቅጽ 1፣ ቅጽ 2፣ ቅጽ 3” መጻህፍቶች ጀምሮ በቅርቡ እስከታተመው እስከ ኮለኔል መንግስቱ ራሳቸው የጻፉት “ትግላችን ቅጽ 2” መጽሀፍ ድረስ በርከት ያሉ በጉዳዩ ዙሪያ የሚያወሱ መጻህፍትን በመዳሰስ ስለ እሳቸው መንግስት የራሳችን ምልከታ አለን። ገና 7ኛ ክፍል ሆነው ቂጣቸውን ሳይጠርጉ የመንግስትን ስልጣን ሲመኙ ከነበሩ የዘመኑ ወጣቶች እስከ የአገሪቱ ዋርካ የሆኑት የስልሳ ሚኒስትሮች ግድያ ያለውን ሁነት ከማንም ባልወገነ መልኩ ገምግመን የራሳችን እሳቤ አለን።





ግንቦት 20፣ 1983 ዓ.ም አዲስ አበባ (4)
እንደ አብዛኛው የእኔ ትውልድ ኢህአዴግ በየሜዲያው የሚደሰኩረውን የደርግን የማጥላላት፣ ራሳቸውን የማግዘፍና የማግነን እንዲሁም ደርግን እንደ ጭራቅ የሚያደርግ ፕሮፖጋንዳ ስንጋት ያደግን ትውልድ ነን። ምንም ቢሆን ግን ከኢህአዴግ መንግስት የደርግ መንግስት ፍፁም የተሻለ ነበር ለማለት እደፍራለሁ። ከደርግ መንግስት የማደንቀው ተግባር እስከነ ችግሩም ቢሆን መሬት በማከፋፈል ጭቁኑን ኢትዮጵያዊ የመሬት ባለቤት ማድረጋቸውና የሃይማኖት እኩልነትን ማምጣታቸው ሲሆን በጣም የምኮንነው ደግሞ የእነዚያ 60 ሚኒስትሮችና የአገር ዋርካዎች ግድያ እና የኢትዮጵያን ህዝብ በጥበብና በብልሀት ሳያታግሉ ለዘረኛውና ከፋፋዩ ለወያኔ/ኢህአዴግ አሳልፈው መስጠታቸው ነው።

No comments:

Post a Comment