Pages

Saturday, June 2, 2018

ግንቦት በኢትዮጵያ ታሪክ


01 Jun 2018
በአጋጣሚም ይሁን ታስቦበት … ግንቦት በኢትዮጵያ ታሪክ በርካታ ድርጊቶች የተፈጸሙበት ወር ነው፡፡ ኢትዮጵያ በግንቦት ወር ታዋቂ ልጆቿን ወልዳለች፤ ወደማይቀረው ዓለምም ሸኝታለች፤ መሪዎቿን ወደ ሥልጣን አምጥታለች፤ ከሥልጣናቸው ሽራለች፤ አስከፊ ጦርነቶችን አስተናግ ዳለች፤ ከነዚህ ታሪካዊ ክስተቶች በተጨማሪ ግንቦት ያልተለመዱ ክስተቶች የተስተናገዱበት ወርም ነው፡፡ ታዲያ ከኢትዮጵያ ታሪክ ጋር ልዩ ቁርኝት ያለውን ይህን ወር ከመሰናበታችን በፊት ኢትዮጵያ በግንቦት ወር ካስተናገደቻቸው ታሪካዊ ክስተቶች መካከል ጥቂቶቹን ብቻ በአጭሩ ለመቃኘት እንሞክር፡፡

ግንቦት የልደት ወር ነው፡፡ ወታደራዊው የደርግ መንግሥት ከወደቀበት ጊዜ ጀምሮ እስከ 2004 ዓ.ም መገባደጃ ድረስ በመጀመሪያ በፕሬዚዳንትነት፣ በመቀጠልም በጠቅላይ ሚኒስትርነት ኢትዮጵያን የመሩት አቶ መለስ ዜናዊ የተወለዱት በግንቦት ወር ነው፡፡ አቶ መለስ ኢትዮጵያ አሁን ያለውን የፌዴራላዊ አስተዳደር ሥርዓት እንድትከተልና ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት ከሚያስመዘግቡ አገራት ተርታ እንድትሰለፍ የአንበሳውን ድርሻ የያዙ ሰው ናቸው፡፡
የገናናው የሸዋ ንጉሥ የንጉሥ ሳህለሥላሴ የልጅ ልጅ፣ የታላቁ ንጉሠ ነገሥት ዳግማዊ ምኒልክ የአክስት ልጅ እንዲሁም የግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ አባት የሆኑት ልዑል ራስ መኮንን ወልደሚካኤል የተወለዱትም በግንቦት የመጀመሪያው ቀን በ1844 ዓ.ም ነበር፡፡ ልዑል ራስ መኮንን ወልደሚካኤል የሐረርጌን ግዛት በማቅናትና በሚገባ በማስተዳደር ለንጉሥ ምኒልክ (በኋላ ዳግማዊ አፄ ምኒልክ) ሀገር የማቅናት ተግባር ብርቱ አጋዥ የሆኑ ሰው ነበሩ፡፡ የዳግማዊ አፄ ምኒልክ ተወካይ በመሆን ሁለት ጊዜ ወደ አውሮፓ ሀገራት የተጓዙት ልዑል ራስ መኮንን፣ ወደ ኢጣሊያ በሄዱ ጊዜም የኢጣሊያ ጋዜጦች የውጫሌ ውልን ምክንያት በማድረግ ኢትዮጵያ በኢጣሊያ መንግሥት ጥገኝነት ስር እንዳለች አድርገው የሚጽፉትን ጽሑፍ በመመልከታቸው ተቃውሟቸውን ለኢጣሊያ መንግሥት ከነገሩ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰው የውሉን መበላሸት ለዳግማዊ አፄ ምኒልክ አሳውቀው ውሉ በይፋ እንዲሰረዝ አድርገዋል።
የውጫሌ ውል ያስከተለው የትርጉም ለውጥ መፍትሄው ጦርነት ሲሆንም ልዑል ራስ መኮንን ሠራዊታቸውን ይዘው ከአምባላጌ እስከ አድዋ በተደረጉት ውጊያዎች ላይ በመሳተፍ ጀግንነታቸውን አስመስክረዋል፡፡ ከቤተ መንግሥት ባለሟልነት ጀምረው በወታደርነት፣ በጦር መሪነት፣ በግዛት አስተዳዳሪነትና በዲፕሎማትነት በፈጸሟቸው አኩሪ ተግባራት ምክንያት ንጉሠ ነገሥት ዳግማዊ አፄ ምኒልክ የዙፋናቸው ወራሽ ሊያደርጓቸው ያስቡ እንደነበር ታሪክ ያስረዳል፡፡
በግንቦት ወር መፈንቅለ መንግሥት የተሞከረ ባቸውና በግንቦት ወር አገር ጥለው የሸሹት የደርግ ሊቀመንበር ሌተናል ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያምም የተወለዱት በግንቦት ወር ነው፡፡
ግንቦት የእረፍት/ሞት ወርም ነው፡፡ በቀዶ ጥገና ህክምና ዘርፍ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ሐኪም የሆኑት ፕሮፌሰር አስራት ወልደየስ ያረፉት በግንቦት ወር 1991 ዓ.ም ነው፡፡ በታዋቂ የውጭ አገራት የሕክምና ሳይንስ ትምህርት ቤቶች የተማሩት ፕሮፌሰር አስራት «የጤና ጥበቃ ሚኒስትርነት ሥልጣንን አልፈልግም፤ የተማርኩት ሐኪም ሆኜ አገሬን ላገለግል ነው» በማለት ወገናቸውን አገልግለዋል፡፡
ከባልደረቦቻቸው ጋር በመሆን የህክምና ማሰልጠኛ እንዲከፈት በተደጋጋሚ ያቀረቡት ጥያቄ ተቀባይነት አግኝቶ የጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ሕክምና ትምህርት ቤትን እውን አደረጉ፡፡ የሕክምና ት/ቤቱ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ዲን ሆኑ፡፡ የጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ሲቋቋምም የቴክኒክ ኮሚቴውን የመሩት እርሳቸው ነበሩ፡፡
ፕሮፌሰር ዶክተር አስራት በወቅቱ በተደጋጋሚ ወደ ዘመቻ የተላኩ ሲሆን፤ የሄዱባቸውንም ዘመቻዎች በብቃትና በክብር ለመወጣት በቅተዋል፡፡ በዚህም መሠረት በ1968 እና በ1969 ዓ.ም በቀዶ-ጥገና ሐኪምነት በቃኘው ሆስፒታል፣ አስመራ፤ በ1970 ዓ.ም በራዛ ዘመቻ በቀዶ-ጥገና ሐኪምነት እና ቡድን መሪነት በመቐለ ሆስፒታል፤ እንዲሁም በሰኔ 1971 ዓ.ም በቀዶ-ጥገና ሐኪምነት ምጽዋ ዘምተው ግዳጃቸውን በብቃት ተወጥተዋል፡፡
ፕሮፌሰር አስራት በህክምናው ዘርፍም «አስራት የተባለ ጸበል ፈልቋል» እስከመባል የደረሰ አንቱታን ያተረፉ ብቁ ሐኪም ነበሩ፡፡ የንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴም የግል ሐኪም ነበሩ፡፡ ፕሮፌሰር ዶክተር አስራት በመንግሥታት የሥራ ኃላፊዎች ይደርስባቸው የነበረውን ከፍተኛ ጫና ተቋቁመው ሀገራቸውን ሳይለቁ ሕዝባቸውን ሲያገለግሉ የቆዩ አንጋፋ ባለሙያ ናቸው፡፡
ገናናውና መናኙ የታላቋ አክሱም ንጉሥ አፄ ካሌብ ያረፉት በግንቦት ወር በ20ኛው ቀን ነበር፡፡ አፄ ካሌብ ከአክሱምና አካባቢው አልፈው ቀይ ባሕርን ተሻግረው የደቡብ አረቢያ ሕዝቦችን ያስገበሩ ታላቅ ንጉሥ ነበሩ፡፡ ከአይሁዳዊው ንጉሥ ፊንሐስ ጋር ያደረጉትን ጦርነት በድል ካጠናቀቁ በኋላም አባ ጰንጠሌዎን ገዳም ገብተው መነኑ፡፡
በኢትዮጵያ ፖለቲካ ታሪክ ስማቸው በጉልህ ከሚጠቀሱት እንስቶች መካከል አንዷ የሆኑት እቴጌ ምንትዋብ ያረፉትም በግንቦት ወር ነው፡፡ የአፄ በካፋ ባለቤት የነበሩት እቴጌ ምንትዋብ፣ ጎንደር የኢትዮጵያ ነገሥታት ማዕከል በነበረችበት ወቅት የነበራቸው ተፅዕኖ ከፍ ያለ እንደነበር ታሪክ ያሳያል፡፡ ባለቤታቸው አፄ በካፋ ከሞቱ በኋላ በተከታታይ በነገሡት በልጃቸው ዳግማዊ አፄ ኢያሱ እንዲሁም በአፄ ኢዮአስ ዘመነ መንግሥታት ትልቅ ሚና ነበራቸው፡፡ ከፖለቲካ ተሳትፏቸው በተጨማሪም ዛሬ ድረስ በበርካታ ጎብኚዎች የሚጎበኙ አብያተ ክርስቲያናትን አሳንፀዋል፡፡ ከዚሁ ከመካከለኛው ዘመን የኢትዮጵያ ታሪክ ሳንወጣ አፄ ሠይፈአርዕድ እና አፄ እስክንድር ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት በግንቦት ወር ነው፡፡
የንጉሠ ነገሥት ዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ ባለቤት እቴጌ ጥሩወርቅ ውቤ ያረፉትም በግንቦት ወር 1860 ዓ.ም ነው፡፡ እቴጌ ጥሩወርቅ የካቲት 3 ቀን 1847 ዓ.ም በደጃዝማች ካሣ ኃይሉ (በኋላ ንጉሠ ነገሥት ዳግማዊ አጤ ቴዎድሮስ) ደረስጌ ላይ የተሸነፉት የደጃዝማች ውቤ ኃይለማርያም ልጅ ናቸው፡፡ እቴጌዋ ያረፉትም ከባለቤታቸው ሞት በኋላ ከልጃቸው ከልዑል ዓለማየሁ ቴዎድሮስ ጋር ወደ እንግሊዝ ሲሄዱ ነው፡፡
አንጋፋውና ዝነኛው ጋዜጠኛ ጳውሎስ ኞኞ ይቺን ዓለም በሞት የተለያት ግንቦት 29 ቀን 1984 ዓ.ም ነው፡፡ የጳውሎስ ኞኞ ስም ሲነሳ ወደአብዛኛው ሰው አዕምሮ የሚመጣው በቀለም ትምህርት ብዙም ሳይገፋ በድፍን ኢትዮጵያ ዝነኛና ተወዳጅ ለመሆን ያበቃው የጋዜጠኝነት ሥራው ነው፡፡ በዘመናዊ ትምህርት አራተኛ ክፍልን ያልተሻገረው ጳውሎስ፣ በተፈጥሮ የታደለው የማንበብ፣ የመጠየቅና የመመራመር ተሰጥኦ በጋዜጠኝነት ሙያው አንቱታን አትርፎለታል፡፡ በኢትዮጵያ ድምፅ ጋዜጣ፣ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት፣ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን እንዲሁም በኢትዮጵያ ራዲዮ ሲሰራ «ጋዜጠኝነትስ እንደጳውሎስ!» የተባለለት ይህ ሰው፣ በርካታ መጽሐፍትንና ቲያትሮችንም ለአንባቢያን አበርክቷል፡፡ «ሁሉን እወቅ፤ የሚሆንህን ያዝ» የሚለው የሐዋርያው ጳውሎስ መልዕክት በውስጡ ሰርፆ እንደነበር በተደጋጋሚ ሲናገር ነበር፡፡ መንገድ ላይ ወድቃ የሚያገኛትን ቁራጭ ወረቀት ሁሉ በማንሳት ማንበብ ልማዱ የነበረው ይህ አስደናቂ ሰው፣ ከአማርኛ በተጨማሪ ሌሎች ቋንቋዎችንም ይናገር ነበር፡፡
ጳውሎስ የፕሬስ ነፃነት እንዲከበር በተባ ብዕሩ ሞግቷል፡፡ ይህ ተጋድሎውም ለማስፈራሪያ፣ ለዛቻና ለእንግልት ዳርጎታል፡፡ ጳውሎስ ጋዜጠኛ ብቻ አይደለም፤ ብዙ የሙያ ዓይነቶችን ከባለሙያዎቹ ባላነሰ መልኩ ይከውን ነበር ይባላል፡፡ ግልፅነት፣ ድፍረት፣ ለወገንደራ ሽነትና ጨዋነትም የጳውሎስ መገለጫዎች እንደነበሩ ብዙዎች ምስክር ናቸው፡፡ ባለውለታችንና «የፊደል ገበታ አባት» ቀኛዝማች ተሥፋ ገብረሥላሴ ግንቦት 26 ቀን 1992 ዓ.ም የመጨረሻ ቀናቸው ነበረች፡፡
ግንቦት የንግሥናና የሹመት ወር ነው፡፡ ዳግማዊ አጤ ምኒልክ ወራሻቸው የልጅ ልጃቸው ልጅ ኢያሱ ሚካኤል መሆኑን በአዋጅ ያሳወቁት ግንቦት በገባ በ10ኛው ቀን በ1901 ዓ.ም ነው፡፡ የልጅ ኢያሱ አባት ራስ ሚካኤል አሊ ደግሞ «ንጉሠ ወሎ ወትግራይ» ተብለው የነገሱት በግንቦት ወር መገባደጃ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢ.ህ.አ.ዴ.ግ) አዲስ አበባን የተቆጣጠረውና ሥልጣን የያዘውም በግንቦት ወር በ20ኛው ቀን በ1983 ዓ.ም ነው፡፡
ግንቦት የሽረት ወርም ነው፡፡ ሊቀመንበር መንግሥቱ ኃይለማርያም አገር ጥለው የሄዱትና ደርግ የወደቀውም በግንቦት ነው፡፡ ግንቦት ለብዙ የጎንደር ነገሥታት የሥልጣናቸው ማብቂያ እንደነበርም በታሪክ ተመዝግቧል፡፡
ደም አፋሳሽ ጦርነቶች የታዩበት ግንቦት፣ የንጉሥ ምኒልክ (በኋላ ዳግማዊ አጤ ምኒልክ) እና የንጉሥ ተክለሃይማኖት ጦር እምባቦ ላይ በግንቦት የመጨረሻው ቀን ከባድ ውጊያ አድርጓል፡፡ የደጋማው ክርስቲያን ነገሥታት እና የግራኝ አሕመድ ጦርነቶች የከፉት በግንቦት ወር ነበር፡፡
የፋሺስት ኢጣሊያ ጦር የደብረ ሊባኖስ ገዳምን ዘርፎ መነኮሳቱን በግፍ የጨፈጨፈውም በዚሁ በግንቦት ወር ነው፡፡
የአፍሪካ አንድነት ድርጅት (የአሁኑ የአፍሪካ ኅብረት) እና የአንጋፋው «አዲስ ዘመን» ጋዜጣ ምስረታ የተከናወ ነው በግንቦት ወር ነው፡፡ እሥራኤል ቤተ-እሥራኤ ላውያንን ከኢትዮጵያ ወደ እሥራኤል ለመውሰድ «ዘመቻ ሰለሞን (Operation Solomon)»ን ያካሄደችው በዚሁ በግንቦት ወር ነው፡፡ በዘመቻ ሰለሞን 14ሺ325 ቤተ-እሥራኤላውያን በ36 ሰዓታት ውስጥ፣ በ35 አውሮፕላኖች ከኢትዮጵያ ወደ እሥራኤል ተወስደዋል፡፡
ፎቶ ግራፍና ኢትዮጵያ/ኢትዮጵያውያንም የተዋወቁት ንጉሠ ነገሥት ዳግማዊ አጤ ምኒልክ ግንቦት 13 ቀን 1875 ዓ.ም በተነሱት የመጀመሪያ ፎቷቸው ነው፡፡
በአጠቃላይ ግንቦት ከኢትዮጵያ ታሪክ ጋር ከተቆራኙ ወራት መካከል አንዱ ነው፡፡ ግንቦት እና ኢትዮጵያ የቀን ምልኪያ አላቸው የሚያስብል ትስስር አላቸው፡፡


No comments:

Post a Comment