Pages

Tuesday, May 22, 2018

‹‹መሥራችና ባለቤት›› እና ‹‹መጤ›› ብሔረሰቦች ግንኙት ከሕገ መንግሥቱ አንፃር

በውብሸት ሙላት
ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የአገራዊ ማንነትና የአገር ግንባታ ጉዳይ ለብዙዎች አጀንዳ እየሆነ መጥቷል፡፡ ጉባዔዎች እየተካሄዱ ነው፡፡ የተወሰኑ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችም ለእነዚህ ጉዳዮች ትኩረት ሰጥተው በመወያየትም ላይ ይገኛሉ፡፡ የተወሰኑ የሬዲዮና የቴሌቪዥን ድርጅቶችም እነዚህን ውይይቶችና የራሳቸውንም ፕሮግራም በማዘጋጀት ለሕዝብ እያስተላለፉ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት ውይይቶችና ዝግጅቶች ከወትሮው በተለየ ትኩረት መሳባቸው የአገር ግንባታ ሒደቱ እንከን አጋጥሞታል የሚል ዕሳቤን መነሻ በማድረግ ይመስላል፡፡
በዚህ ጽሑፍ ካጋጠሙት ከእንከኖቹ መገለጫ ከመንስዔዎቹ ደግሞ አንዱን እንመለከታለን፡፡ አንዱ ለሌላው የመንስዔና ውጤት ግንኙነት ስለሚኖረው ነው፡፡  አገራዊ ማንነት ግንባታው ላጋጠሙት እንከኖች ማሳያ የሚሆነው ከየክልሎቹ እየተደረገ ያለው መፈናቀል ነው፡፡ የሚፈናቀሉት ደግሞ መጤ የሚባሉት ብሔሮች ናቸው፡፡ እንዲህ ዓይነቱን የመጤነት ፍረጃና የማፈናቀል ተግባር የአባባሽነት ሚና ያላቸውን የክልል ሕግጋት በአስረጅነት እናነሳለን፡፡
በፌዴራሉ ሕገ መንግሥት እንደተገለጸው ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ትርጉማቸው ተመሳሳይ ነው፡፡ ራሳቸውን የማስተዳደርና በማዕከላዊው መንግሥት ዘንድም ሚዛናዊ የሆነ ውክልና የማግኘት መብት አላቸው፡፡
የፌዴራሉ ሕገ መንግሥት አንድ ዓይነት ትርጉም እንዲኖራቸው በማድረጉ ተዋረዳዊ የሆነውን አረዳድ ለማስወገድ ሞክሯል፡፡ አንቀጽ 39 ላይ የተዘረዘሩትን መብቶች ከመጠቀምና የኢትዮጵያ የልዑላዊነት ባልተቤት ከመሆን አንፃር በሕግ ምንም ልዩነት አልተቀመጠም፡፡
እንደ እነ ሌኒንና ስታሊን አስተምህሮ የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 39 ቢቀረጽ ኖሮ ግን የመገንጠል መብት የሚኖራቸው የተወሰኑት ይሆኑና ሌሎቹ ደግሞ ለአቅመ ብሔርነት ሲደርሱ ነበር ይኼንን መብታቻውን ማስከበር የሚችሉት፡፡ ራስ ገዝ መሆን የሚችሉትም እንደዚያው ነው፡፡ በመሆኑም ከላይ በተገለጠው መንገድ፣ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እኩል ናቸው፡፡ አንድ ናቸው፡፡ ሁሉንም መብቶች በሚመለከት ተመሳሳይ መብት አላቸው፡፡
ምንም እንኳን እኩል መብት እንዳላቸው ቢገለጽም በክልል ካላው አተገባበር የምንረዳው የተለያዩ መሆናቸውን ነው፡፡ እርግጥ ነው በሕግ የተለያየ ትርጉም ቢሰጣቸው የብሔር እኩልነትን ይንዳል፡፡ በሕገ መንግሥቱ ማስፈን የታሰበው  እኩልነትን እንጂ ልዩነትን ወይም ተዋረዳዊነትን ማምጣት አይደለም፡፡ በሌላ ጎኑ ደግሞ ለሁሉም ገቢራዊ የሆነ እኩልነትን ለማምጣት ከሰማንያ በላይ ክልል መመሥረትና የመሳሰሉትን መተግበር አዳጋች ነው፡፡
የክልል ሕገ መንግሥቶችን ስንቃኝ ቢያንስ ብሔርና ብሔረሰብን በመለየት እንዳስቀመጡ እንረዳለን፡፡ የትግራይ ሕገ መንግሥት ትግሬን ብሔር ሲል ኢሮብና ኩናማን ብሔረሰቦች፣ የአማራ አማራን ብሔር ብሎ ሲጠራ አዊ፣ ኻምራንና ኦሮሞን ብሔረሰብ፣ የኦሮሚያ ኦሮሞን ብሔር፣ የኢትዮጵያ ሶማሊያ ሶማሌን ብሔር፣ የጋምቤላ አምስቱንም ብሔረሰብ ሲል፣ የሐረሬም ሐረሬን ብሔረሰብ ይላል፡፡ የሌሎቹም ተመሳሳይ ነው፡፡
ሦስትነታቸው በዋናነት የሚመነጨው ከክልል ሕገ መንግሥታትና ከተግባር ነው፡፡ የፌዴራሉ ሕገ መንግሥት ለሦስቱም ቃላት አንድ ትርጉም ከመስጠት የዘለለ ልዩነታቸውን የሚያስረዳ ነገር አላስቀመጠም፡፡ ይሁን እንጂ የቅደም ተከተላቸው አቀማመጥ ተዋረዳዊ መሆን የሚያሳየው ፍንጭ አለ፡፡
‹‹አናሳ ብሔረሰቦች›› የሚል አንድ ሐረግ በአንቀጽ 54(3) ላይ መግለጹም እንደዚሁ፡፡ አናሳ ብሔር አላለም፡፡ ብሔር ከሆነ አናሳ አይሆንም ሊሆን ይችላል፡፡ በእርግጥ አናሳ ሕዝብም አላለም፡፡ የመረጠው ብሔረሰብን ብቻ ነው፡፡ አንዱን ብቻ ለማመልከት ቢሆን ኖሮ ከላይ በተገለጸው ተዋረዳዊ አካሔድ መሠረት አናሳ ብሔረሰብና ሕዝቦች ሊል ይችል ነበር ብሎ መተርጎም ይቻላል፡፡ ምክንያቱም ሕዝብ ከብሔረሰብ በታች ነውና! ሁሉንም ለማመልከት ነው እንዳንልም ለምን እንደወትሮው አናሳ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦችም አላለም? ብሎ መጠየቅም ይቻላል:: ወይም ደግሞ በሌሎች ሥነ ጽሑፎች የተለመደውን ቃል ለመጠቀም ነውም ማለት ይቻላል፡፡ ቢያንስ የተለያዩ ለመሆናቸው ግን ጠቋሚ ነው፡፡
የተለያዩ ስለመሆናቸው ከክልል ሕገ መንግሥታትም መረዳት ይቻላል ብለናል፡፡ ምክንያቱም ከላይ እንደተገለጸው በአማራ ክልል አማራን ብሔር፣ ቀሪዎቹን ብሔረሰቦች ብሎ ይጠራል፡፡ ሌሎቹም እንደዚያው፡፡ እነዚህ ብሔር ተብለው የተጠሩት ክልል መሥርተዋል፡፡ በስማቸው ክልል ተሰይሟል፡፡ በትግራይ ክልል ቢያንስ ነባሮቹ የክልሉ ተወላጅ የሆኑት ኩናማና ኢሮብ ቢኖሩም፣ የክልሉ ስም የትግራይ ክልል ተብሎ ነው የተሰየመው፡፡ ሁለቱን አያካትትም፡፡ በአማራ ክልልም እንደዚያው፡፡ በአፋርም ቢሆን ለአርጎባዎች ልዩ ወረዳ እንደሚኖራቸው ሕገ መንግሥቱ ቢገልጽም፣ የክልሉ ስም ያው የአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ተብሎ ነው የሚጠራው፡፡
እንግዲህ ይህ ተዋረዳዊ አሰያየም በራሱ የአገር ግንባታ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ መፍጠሩ አይቀሬ ነው፡፡ ከዚህ በባሰ ሁኔታ የአገር ግንባታ ሒደቱ ላይ ከፍ ያለ አሉታዊ ተፅዕኖ የሚፈጥረው ግን በተለያዩ ክልሎች ተሰራጭተው የሚገኙት ብሔሮች፣ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ነባር ከሚባሉት ጋር ያላቸው ግንኙነት ነው፡፡ ግንኙነት በምንልበት ጊዜ በሕግ የተቀመጠውን ብቻ ነው ትኩረታችን፡፡ ሕጉ ይዞት የሚመጣው ጣጣ ስላለ በዚሁ ላይ እንወሰናለን፡፡ ይህንን ሁኔታ ለማስረዳት ደግሞ የቤኒሻንጉል ጉሙዝና የጋምቤላ ክልሎችን ሕግጋተ መንግሥት ዋቢ እናደርጋለን፡፡ ከዚያም የሦስት ክልሎችን የከተሞች አዋጆች እንጨምራለን፡፡ ሁኔታውን የበለጠ ለመገንዘብ በእነዚህና በሌላም ክልል የሚኖረውን የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ጥንቅር እናያለን፡፡
እንግዲህ ከፌዴራሉ አጠራር ለየት ያለ ብሔር፣ ብሔረሰቦችንና ሕዝቦችን በተመለከተ በጋምቤላና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሕግጋተ መንግሥታት ላይ እናገኛለን፡፡ የጋምቤላ ሕገ መንግሥት በክልሉ የሚገኙትን ነባር ብሔር ብሔረሰቦች ‹‹መሥራች አባላት›› በማለት ሲጠራቸው  የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ደግሞ ‹‹የክልሉ ባለቤት ብሔረሰቦች›› የሚሉ ሐረጋትን ይጠቀማሉ፡፡ ከእነዚህ ሕግጋተ መንግሥታት የምንረዳው መሥራች ያልሆኑና ባልተቤት ያልሆኑ ብሔሮችና ብሔረሰቦች እንዳሉ ነው፡፡
 በግልጽ በጽሑፍ ሁለቱ ክልሎች መሥራችም ይሁን ባልተቤት ይበሉ እንጂ ቀሪዎቹም ክልሎች ቢሆኑ የተከተሉት ይኼንኑ አካሄድ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ምክንያቱም የትግራይ ክልል የትግሬ፣ የኢሮብና የኩናማ፣ የአፋር ደግሞ አፋርና አርጎባ እያለ እየዘረዘሩ ይቀጥላሉ፡፡ የተለያዩ ብሔር፣ ብሔረሰብና ሕዝቦች መብቶችን እንደቡድን የሚያጎናጽፉት ያው ዞሮ ዞሮ ለነባሮቹ ብቻ ነው፡፡
እንደውም መሥራችና ባለቤት ላልሆኑት በክልሉ በተለያዩ መዋቅሮች ውስጥ ስለሚወከሉበት ሁኔታ ሕግ እንደሚወጣ በዚያ መሠረት እንደሚፈጸም እነዚህ ሁለት ሕግጋተ መንግሥታት ዋስትና ይሰጣሉ፡፡ ይህ ከሌሎቹ የተሻሉ ያደርጋቸዋል፡፡ ነባር ያልሆኑት የሚወከሉበት ሥርዓትን ለመዘርጋት የተደረገ ነው፡፡ ከዚህ (ከውክልና) አንፃር በተለይ ከፍተኛ ነባር ያልሆኑ ሕዝቦች ከሚገኙባቸው ከሐረርና ኦሮሚያ ክልሎች በእጅጉ ይሻላሉ፡፡
የሆነው ሆኖ በተለይ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ ጋምቤላና የሐረሪ ክልሎች ካላቸው የብሔረሰቦች ስብጥር አንፃር ሲታይ ከእንደገና መጤን ያለባቸው ጉዳዮች ያሉ ይመስላል፡፡ እስኪ ስብጥሩን እንመልከተው፡፡
ይህ አኀዝ በ1999 ዓ.ም. ከተደረገው አገር አቀፍ የሕዝብና ቤት ቆጠራ ውጤት ነው የተወሰደው፡፡ ባለፉት አሥራ አንድ ዓመታት የሕዝብ ቁጥሩ ከዚህ የመብለጡ ነገር ከግምት ይግባ፡፡
በቆጠራው መሠረት የቤኒሻንጉል/ጉሙዝ ክልል ውስጥ ከሚኖሩት ብሔሮች ወይም ብሔረሰቦች በርከት ያለ ቁጥር ያላቸውን እንመልከት፡፡ የክልሉ ጠቅላላ ነዋሪ ብዛቱ 784,345 ነው፡፡ ከዚህ ውስጥ በርታ 199,303፣ አማራ 170,132፣ ጉሙዝ 163,781፣ ኦሮሞ 106,273፣ ሽናሻ 60,587፣ ማኦ 15,384፣ ኮሞ 7,773፣ ትግራዋይ 5,562 ሲሆኑ ከዚህ በታች ቁጥር ያላቸውም አሉ፡፡ ይሁን እንጂ የክልሉ ባለቤት ብሔረሰቦች ተብለው ዕውቅና የተሰጣቸው በርታ፣ ጉሙዝ፣ ሺናሻ፣ ማኦና ኮሞ ናቸው፡፡
የጋምቤላ ክልልን በምናይበት ጊዜ ደግሞ የክልሉ ጠቅላላው ነዋሪ 307,906 ሲሆን ከዚህ ውስጥ ኑዌር 143,286፣ አኙዋክ 64,986፣ አማራ 25,862፣ ከፍቾ 15,490፣ ኦሮሞ 14,833፣ መዠንግር 12,280፣ ሸክቾ 6,976፣ ከምባታ 4,410፣ትግራዋይ 4,052፣ ኡፖ 990፣ ማኦ 64 ሲሆኑ አራት ብሔረሰቦች ደግሞ ከአንድ ሺሕ በላይ ቁጥር አላቸው፡፡  ይሁን እንጂ የክልሉ መሥራች ብሔረሰቦች ኑዌር፣ አኙዋክ፣መዠንግር፣ ኡፖ እና ማኦ ናቸው፡፡ የማኦዎቹ ከቁጥሩ ማነስ ባለፈ ቤኒሻንጉልም ውስጥ ባለቤት ብሔረሰብ ናቸው፡፡
የሐረሪ ክልል ደግሞ ይህን ይመስላል፡፡ የክልሉ ጠቅላላ ነዋሪ ብዛት 183,415 ነው፡፡ ከዚህ ውስጥ  ኦሮሞ 103,468፣ አማራ 41,768፣  ሐረሪ 15,863፣ ሲሆን ጉራጌና ሶማሌ ይቀጥላሉ፡፡ የክልሉ ሕገ መንግሥት መሥራች ወይም ባለቤት ብሔረሰብ የሚል አጠራር ባይኖረውም፣ አስተዳደር ላይ የሚሳተፉት ግን ሐረሪና ኦሮሞ ብቻ ናቸው፡፡
ብዙ ጊዜ እነዚህ ሁለት ክልሎች (ጋምቤላ እና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ) የተጠቀሙበትን አጻጻፍ ከነባር ሕዝቦች (Indigenous Peoples) አኳያ የመተንተንና ለማስረዳት የሚደረግ ሙከራ ይስተዋላል፡፡ በተለይም በዓለም አቀፍ ደረጃ ነባር ሕዝቦችን በሚመለከቱ ከወጡ መግለጫዎችና ልማዳዊ ሕጎች አንፃር የሚኖራቸውን መብቶች ለመዘርዘርም ጥረት ይደረጋል፡፡ ይሁን እንጂ ከላይ በገለጽኩት ምክንያት ሁሉም ክልሎች በግልጽ ባያስቀምጡም፣ የየራሳቸው ነባር ሕዝቦች አሏቸው፡፡ ትርጓሜውም ከዓለም አቀፉ አረዳድ ፈጽሞ የተለየ ነው፡፡
ከዓለም አቀፍ ሕግጋት መረዳት እንደሚቻለው ነባር ሕዝቦች በወረራ፣ በቅኝ ግዛት ወይም በአገር ምሥረታ ምክንያት መሬታቸውን የተነጠቁ፣ ለድህነት የተጋለጡ፣ የተገለሉ ሕዝቦች ናቸው፡፡ ከእነዚህ ድርጊቶች በፊት በቦታው የሚኖሩ ከአንድ ዝርያ የመነጩ፣ በሕግ እና/ወይም በተግባር የተጨቆኑ ነገር ግን ባህላቸውን፣ አስተዳደራቸውን፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ መሠረታቸውን ለመጠበቅ ሁልጊዜ የሚጥሩ ሕዝቦች ናቸው፡፡ ላለመቀላቀልና መሬታቸው ላይ በሰፈሩት ሕዝቦች ባህል ላለመዋጥ የሚታገሉም ጭምር፡፡
እነዚህ ነባር ሕዝቦች በዓለም አቀፍ ሕግ አምስት መለያ ባሕርያት አላቸው፡፡ ከሌሎች ልዩ መሆን፣ ከመሬታቸው መፈናቀል፣ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ የራሴ የሚሉት መሬት መኖር፣ በመሬታቸው ላይ ቀዳሚ ነዋሪነት እንዲሁም ከፖለቲካው ዓለም የተገለሉ መሆንን እንደመስፈርት ይወስዷቸዋል፡፡ ከዚህ አንፃር የአውስትራሊያ አቦርጂናሎች፣ የኒውዚላንድ ማኦሪዎች፣ የኖርዲኮቹ ሳሚዎች ለዚህ ምሳሌ ናቸው፡፡
እንደዚህ ዓይነት ሕዝቦች የሚኖሩባቸው አገሮች መንግሥታትም በተቀናጀ ሁኔታ መብቶቻቸው እንዲከበር፣ ማንነታቸው እንዲጠበቅ፣ ባህሎቻቸው እንዲጎለብቱ ወዘተ የማድረግ ግዴታ አለባቸው፡፡ ወንጀል ፈጽመው ሲቀጡ እንኳን ከእስራት በመለስ ያሉ ሌሎች የቅጣት ዓይነቶች እንዲሆኑ ነው የሚጠበቀው፡፡ በተለይ የመሬት ባለቤትነታቸውም መረጋገጥ አለበት፡፡
ከላይ የተገለጹት በእኛ አገር የፌዴራል ሥርዓት ውስጥ ተፈጻሚ አይሆኑም፡፡ ምክንያቱም ሁሉም ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በጋራም ይሁን በተናጠል የራሳቸው ክልል ስላላቸው ከላይ የተገለጹትን አያሟላም፡፡ በየክልሉ ከነባሮቹ ሌላ ሁሉን ነገር የተቆጣጠረ ሕዝብ መኖርን ይጠይቃል፡፡ ጥረቱም ነባሮችን ከሌላው እኩል ለማድረግ እንጂ ሌሎቹን በማግለል አይደለም፡፡ የክልል ሕገ መንግሥታትም ይሁኑ የፌዴራሉ ዓላማቸው በዋናነት ነባሮቹን ነባር ካልሆኑት እኩል ለማድረግ አይደለም፡፡ ማለትም ነባር ያልሆኑት አብዛኛውን የፖለቲካም ይሁን የኢኮኖሚ መዋቅር ይይዙትና ነባሮቹ ባሉበት (በብዙ አገሮች ተገልለው በአንድ ቦታ ነው የሚነኖሩት) ስፍራ እንዲቀጥሉ ነው የሚደረገው፡፡
የተወሰኑትን መሥራችና ባለቤት ወይም ነባር ሌሎችን ደግሞ መጤ ማለት አለበለዚያም የመጤነት ስሜት እንዲሰማቸው ማድረግ የጋራ አገር ግንባታ ላይ በጎ ሚና ሊጫወት አይችልም፡፡ ነባርነትና መጤነት የፖለቲካ መቆራቆሻ ነው፡፡ ጥል አንጋሽ ነው፡፡ በተለይም ነባሩ መሬቱንና አገሩን ከደሙ ጋር በማያያዝ እናት አገሬ ወይም አባት አገሬ፣ እትብቴ የተቀበረበት መንደሬ ወይም ቀዬዬ በማለት ሲጠራና ለልጅ ልጅ ለማስተላለፍ ሌሎች እንዳይነጥቁት ሲታገል ነው የሚስተዋለው፡፡ በዚህ መካከል የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች መከሰታቸው አይቀሬ ነው፡፡ የእኛንም አገር ሰንጎ የያዛት አንዱ ችግር ይኼ ነው፡፡
በእርግጥ ኢሕአዴግ ስለ ዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ በሚያትትበት የፖሊሲ ሰነዱ ላይ በመጤዎችና በነባር ሕዝቦች በሚል መነሻ ልዩነት በማድረግ እንደማይቻል ይገልጻል፡፡ ከዚህ ፖሊስም ሆነ ከፌዴራሉ ሕገ መንግሥት ጋር አብሮ በማይሄድ መልኩ አድልኦና መገለልን ሕጋዊ ያደረጉ አዋጆች በተለያዩ ክልሎች ፀድቀዋል፡፡ ለእዚህ ደግሞ የከተማ ምክር ቤቶች ምርጫን በምሳሌነት እንመልከት፡፡
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ የከተሞች ማዕከላትን ለማቋቋና ሥልጣናቸውን ለመደንገግ በወጣው አዋጅ ላይ እንደተገለጸው ለከተማ ምክር ቤት በሚደረደግ ምርጫ ከምክር ቤቱ መቀመጫ ውስጥ 55 በመቶው ለክልሉ ነባር ሕዝቦች የተተወ ነው፡፡
ተመሳሳይ ስያሜ በተሰጠው አዋጅ የኦሮሚያ ክልል ቢሆን 50 በመቶ ለከተማው ኦሮሞ፣ 20 በመቶ በገጠር ገንዳዎች (ቀበሌዎች) ለሚኖሩ ኦሮሞዎች ብቻ ተለይቶ ተቀምጧል፡፡ ያውም ይህ የሆነው ቀድሞ 30 በመቶ ለከተማው አምስት በመቶ ለገጠር ገንዳዎች የነበረውን በመጨመር ነው፡፡ 
በደቡብ ክልል ደግሞ በልዩ ወረዳና ዞኖች ውስጥ ለሚገኙ ከተሞች ለነባር ሕዝቦቹ 30 በመቶ ተቀምጧል፡፡ እነዚህ የሚወዳደሩበትን ምክር ቤት የሥራ ቋንቋ ማወቅ አለማወቅ እንኳን እንደ መስፈርት አልወሰዱትም፡፡ የፌዴሬሽን ምክር ቤት በአንድ ወቅት የወሰነው ግን የሚወዳደርበትን ምክር ቤት ቋንቋ የሚችል ማንም ሰው የመወዳደር መብት አለው በማለት ነው፡፡
እዚህ ላይ አንድ ጥያቄ ማንሳት ተገቢ ነው፡፡ ክልሎች የምርጫ ሕግ የማውጣት ሥልጣን ቀድሞውንስ አላቸው ወይ? የሚለውን፡፡ በሌላ አገላለጽ በሕገ መንግሥቱ በአንቀጽ 51(15) መሠረት የፌዴራል መንግሥት ሥልጣንና ተግባር አይደለም ወይ? እንደማለት ነው፡፡ በዚህ አንቀጽ መሠረት የምርጫና የፖለቲካ መብቶችን የሚመለከቱ ሕጎችን የማውጣት ሥልጣን የተሰጠው የፌዴራሉ መንግሥት ነው፡፡
የአዋጆቹ አርዕስት የከተማ አስተዳደርን የሚመለከት ቢሆንም ውስጡ ስለምርጫ ይደነግጋል፡፡ ክልሉ የሚያወጣውን ሕግ ምርጫ ቦርድ የማስፈጸም ኃላፊነት አለበትን? የሚል ተያያዥ ጥያቄም ማንሳት ይቻላል፡፡ ተጠሪነቱ ለፌዴራሉ ሕዝብ ተወካዮች ሆኖ ነፃነቱና ገለልተኝነቱ ላይ ሳንካ እንዳይኖር (በመርህ እንጂ በተግባር ለማለት አይደለም) ታስቦ የተቋቋመ፣ ደንብ እንኳን ሳይቀር እንደሌሎች ጉዳዮች የሚኒስትሮች ምክር ቤት ማውጣት የማይቻልበት ተቋም፣ ክልሎች እንዳሻቸው ሕግ እያወጡ እንዲያስፈጽም የማድረግ ሥልጣንስ አላቸው ማለት አስቸጋሪ ነው፡፡ የክልል ምርጫ ቦርድ የሚባል ስለሌለ የፌዴራሉ ቅርንጫፎች ብቻ ናቸው በየክልሉ ያሉት፡፡
የከተማውን ምክር ቤት የሥራ ቋንቋ እስከቻሉ ድረስ በብሔር አፋር፣ አማራ፣ ወላይታ፣ ሲዳማ ቢሆኑ ባይሆኑም መወዳደር እየቻሉ እነዚህ ሕጎች ከፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔ፣ ከሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 25 እና 38 አኳያ አብሮ የመሄዳቸው ነገር አጠያያቂ ነው፡፡ መልሶ የዜጎች መብት ላይ ቅርቃር ሆነዋል፡፡ ፖሊሲና ሕገ መንግሥት ሌላ፣ የክልል ሕጎች ደግሞ ሌላ፡፡
የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 25 እና 38 መንፈስ በመነሳት ማንኛውም ኢትዮጵያዊ የትም ይኑር የትም፣ ቋንቋው የፈለገውም ቢሆን መራጩ እስከመረጠውና እስከፈለገው ድረስ የመመረጥ መብት አለው ማለት ይቻላል፡፡ ዋናው የመራጮች ፍላጎት እንጂ የምክር ቤት የሥራ ቋንቋ አይደለም፡፡ በአስተርጓሚ መስማትና መናገር ስለሚቻል፡፡ ከዚህ አንፃር ማንም ሰው ያለምንም የቋንቋ እንቅፋት የመመረጥ ሕገ መንግሥታዊ መብት አለው፡፡ ከዚህም ባሻገር የማንኛውንም የብሔር አባላት ያለ አድልኦ መራጩ እስከፈለገና ጥቅማችንን ያስጠብቅልናል እስካሉ ድረስ የፈለጉትን መምረጥ የእነሱው ኃላፊነት ነው፡፡ ትችቱ ብዙ ‹‹መጤዎች›› በበዙባቸው ከተማዎች ላይ ነባሩ ሕዝብ እንዲዋጡ ያደርጋል፣ ራሳቸውንም  የማስተዳደር መብት ይጋፋል የሚል ነው፡፡
ከላይ የገለጽነው እንዳለ ይሁንና የፌዴሬሽን ምክር ቤት ወደወሰነው ውሳኔ እንመለስ፡፡ ለፌዴራሉ ምክር ቤትና የክልሉ የሥራ ቋንቋ አማርኛ ለሆኑት ለአማራ፣ ለደቡብ፣ ለጋምቤላ፣ ለቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች ምክር ቤት የሚወዳደር ማንኛውም ኢትዮጵያዊ፣ አማርኛ ቋንቋን መቻል ቅድመ ሁኔታ ነው፡፡ የክልሉ ምክር ቤት የሥራ ቋንቋም አማርኛ ያልሆኑት ትግራይ፣ አፋር፣ ኦሮሚያ፣ ሐረርና የኢትዮጵያ ሶማሊያም ለውድድር አስፈላጊው እነዚህን ቋንቋዎች መቻል እንጂ የብሔር ልዩነት አይደለም ማለት ነው፡፡ በዚህ መንገድ አብዛኛው ሰው የተወሰኑ ቋንቋዎችን ብቻ በማወቅ አንድነትን ለማጠናከር ይረዳል ማለት ነው፡፡
በመሆኑም ከላይ የተጠቀሱት ሕጎች ከዚህ ውሳኔ አንፃር ሕገ መንግሥታዊነታቸውም ይሁን ከውሳኔው ጋር አብሮ መሄዳቸው ሊፈተሽ ይገባዋል፡፡ በተለይ ደግሞ ነባር ከሚባሉት ሕዝቦች አንፃር የሌሎቹ ቁጥር ከፍ ያለ በሆነባቸው ክልሎች እንዲህ ዓይነት አዋጆችን ማውጣት ፍትሐዊነትም ይጎድለዋል፡፡ የአገር ግንባታ ሒደትም ላይ አሉታዊ ተፅዕኖው የጎላ ነው የሚሆነው፡፡
በጥቅሉ ሲታይ ለአገር ግንባታ ሒደቱ ሳንካ የሚሆኑ የክልል ሕገ መንግሥታትን እንዲሁም አዋጆችን መከለስ ይገባል፡፡ እንዲህ ዓይነት ሕግጋት ሁለት ዓይነት ዜጎችን ይፈጥራል፡፡ ለማፈናቀልም በማትጊያነት ያገልግላል፡፡

No comments:

Post a Comment