Pages

Tuesday, May 29, 2018

የፖለቲካ ለውጡ የፈነጠቀው ተስፋ ይኖር ይሆን?


አለማየሁ አንበሴ

• ጠ/ሚኒስትሩ የሚያነሷቸው ሀሳቦች ለሃገራዊ መግባባት ጠቃሚ ናቸው
• ሥር ነቀል የምርጫ መዋቅራዊና አስተዳደራዊ ለውጥ ያስፈልጋል
• በቅድመ ሁኔታ ላይ የታጠረ ድርድር አያስፈልግም


   የአገሪቱ የፖለቲካ ድባብ እየተለወጠ ይመስላል፡፡ በሺዎች የሚቆጠሩ የፖለቲካ እስረኞች ተፈተዋል፡፡ አሁንም እየተፈቱ ነው፡፡ ዶ/ር ዐቢይ አህመድ የጠ/ሚኒስትርነት መንበሩን ከያዙ ወዲህ መንግስት የተቃዋሚ ፖለቲካ ሃይሎችን የሚመለከትበት መነጽር በእርግጥም ተለውጧል፡፡ በአገር ውስጥ በሰላማዊ መንገድ ለሚንቀሳቀሱት ምቹ ምህዳር ለመፍጠር መንግስት ቁርጠኝነቱ እንዳለው ጠ/ሚኒስትሩ መግለጻቸው ይታወቃል፡፡ በውጭ አገር ለሚገኙ የፖለቲካ ኃይሎችም  ጥሪ ሲደረግ መቆየቱ አይዘነጋም፡፡ በዚሁ መሰረትም የኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ግንባር መሥራችና ሊቀ መንበር  አቶ ሌንጮ ለታና የድርጅቱ  አመራሮች ሰሞኑን አዲስ አበባ ገብተዋል፡፡ መግባት ብቻም ሳይሆን ከጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ጋር ተገናኝተው ተደራድረዋል፡፡  በትጥቅ ትግል ላይ ያሉ ሌሎች የፖለቲካ ሃይሎችም ነፍጥ ጥለው፣ ወደ አገራቸው በመግባት፣በሰላማዊ መንገድ የፖለቲካዊ ትግላቸውን እንዲቀጥሉ ሰሞኑን ጭምር መንግስት ጥሪ እያቀረበ ነው፡፡
  ለመሆኑ እነዚህ ሁሉ አዎንታዊ የፖለቲካ ለውጦች በአገሪቱ የፖለቲካ ሥርዓትና የዲሞክራሲ ግንባታ ላይ ምን አስተዋጽኦ አላቸው? በአገር ውስጥ ያሉ ተቃዋሚዎችና ፖለቲከኞች   ሂደቱን እንዴት ያዩታል? የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ፤አንጋፋ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮችን አነጋግሮ ሃሳባቸውን እንደሚከተለው አጠናቅሮታል፡፡



     “ጥያቄዎች የሚመለሱ ከሆነ ድርድር ላያስፈልግ ይችላል”
         (አቶ ግርማ ሠይፉ፣ የቀድሞ ፓርላማ አባል)


    ብዙዎች ዶ/ር አብይ የንግግር ሠው ናቸው ይላሉ፤ እኔ በዚህ አልስማማም፡፡ ንግግር ብቻ አይደለም፣ በተግባርም እየተገለጡ ነው፡፡ ግን ሁሉንም በአንድ ጊዜ ያድርጉ የሚል ሰው ካለ፣ ራሱ ሞክሮ ነው ማየት ያለበት፡፡ እስከ ዛሬ ከምናውቀው በተለየ በእስር ቤት ሲማቅቁ የነበሩ ኢትዮጵያውያን እንዲፈቱ ማድረግ ቀላል አይደለም፤ እውቅና መስጠት ያስፈልጋል። ከዚህ በመለስ ለፖለቲከኞች የሚያሣዩትን ክብርና የሚያስተላልፉትን ጥሪ እንደ ትንሽ ነገር መቁጠር፣ ለኔ ትንሽነት ይሆንብኛል፡፡ የፖለቲካ ለውጥ ከተባለም፣ የግድ እኛ ስልጣን ይዘን ማድረግ የለብንም፡፡ ጉዳዩ እንዲፈፀም እንጂ እኛ ስልጣን ላይ ወጥተን ካልፈፀምነው አይጥምም ማለት ጥሩ አይደለም፡፡ እርግጥ ነው ብዙ መሻሻል ያለባቸው ነገሮች ይቀራሉ። እነዚህ የሚቀሩ ጉዳዮች ላይሻሻሉ ይችሉም ይሆናል። ተወዳድረን ስልጣን ይዘን ልንፈፅማቸው የሚችሉ ይሆናሉ፡፡ የፖለቲካ መሻሻል ሂደት ነው፡፡ ግን ቅድሚያ እንዲሻሻሉ የምንፈልጋቸው ነገሮች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ለምሣሌ ግንቦት 7፣ ኦነግ---የሚባሉት ሃይሎች የትጥቅ ትግል  ትተው፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ለመታገል ፍላጎት ማሳየት አለባቸው፡፡ እነሱ ይሄን ፍላጎት ሲያሣዩ ደግሞ እዚህ ያለውም መንግስት ዋስትና ሊሠጣቸው ይገባል። ይሄን ስል አሁን ፖለቲካችን ሊታመን የሚችልበት ደረጃ ላይ ደርሷል ማለቴ አይደለም፡፡ የዶ/ር አብይ መነሣሣት የግለሰቡ የራሣቸው ብቻ ነው ወይስ በአጠቃላይ የግንባሩ ነው? የሚለውን ለማረጋገጥ ጊዜ ሊወስድብን ይችላል፡፡
እኔ ለለውጡ ድርድር ራሱ ላያስፈልገን ይችላል የሚል አመለካከት ነው ያለኝ፡፡ በድርድር ልናገኛቸው የምንችላቸውን ነገሮች እነሱ የሚሠጡን ከሆነ ድርድር ለምን ያስፈልጋል? እኔ ተደራድሬ ነው ያመጣሁት ለማለት ካልሆነ በስተቀር ጥያቄዎች በቀጥታ የሚመለሱ ከሆነ መደራደር ላያስፈልገን ይችላል። ለምሣሌ ተደራድረን እስረኛ ማስፈታት እንፈልግ ነበር፤ ነገር ግን እስረኞች እየተፈቱ ነው፡፡ ምርጫ ቦርድ በሚፈለገው መጠን ከተስተካከለ የግዴታ መደራደር አያስፈልግም።
ስለዚህ ወደ ሃገር ውስጥ እየገቡ ያሉ የፖለቲካ ድርጅቶች መምጣታቸው በበጎ የሚታይ ነው፡፡ ለሃገራዊ መግባባቱም አስፈላጊ ነው፡፡ አሁን ዶ/ር አብይ የጀመሩትን እየደገፍን፣ አክራሪ ሃይሎች እንዳያንሰራሩ መስራት ይጠበቅብናል፡፡ ይህን ስል እነ ዶ/ር አብይ የሚፈለገውን ለውጥ እንዲያመጡ ግፊት ማድረግ እንዳለብን ሳንዘነጋ ነው፡፡
አሁን የእነ ሌንጮ ለታ ኦዴግ ከመጣ፣ እነ ግንቦት 7፣ እነ ኦነግ፣ እነ ኦብነግ እና ሌሎችም ድርጅቶች የማይመጡበት ምክንያት አይኖርም፡፡ እነሱም የፈለጉትን ሃሣብ ለኢትዮጵያ ህዝብ አቅርበው  ህዝቡ ይወስናል ማለት ነው፡፡


--------


           “የፖለቲካ ሃይሎች መምጣታቸው ለህዝብ አማራጭ ይሰጣል”
              (ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ፣ የፖለቲካ ተንታኝ)

   ከተለያዩ የፖለቲካ ሃይሎች ጋር ለመደራደር ፍላጎት እንዳለ ፍንጭ የታየው በኦህዴድ መግለጫ ላይ እንደነበር ይታወሳል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩም በዚህ ረገድ ብዙ ቃል ገብተዋል፡፡ ጥሪም አቅርበዋል። አሁን ቃሉ በተግባር ከተፈፀመ በኔ እይታ ጥሩ ነገር ይመጣል።
እኔ የእስካሁኑን እንቅስቃሴዎች በአዎንታዊ መልክ ነው የማያቸው፡፡ ለሁሉም ድርጅቶች፤ “በር ተከፍቶላችኋልና ሃገር ቤት ገብታችሁ ስሩ” ሲባል ነበር። የኦሮሚያ ፕሬዚዳንት አቶ ለማ መገርሳም፣ “እኛ ሀገር ቤት ቢሮ ለቢሮ፣ ሌሎች ጫካ ለጫካ የሚንቀሳቀሱበት ሁኔታ ማብቃት አለበት” ብለው ነበር፡፡ “ሁሉም በዲሞክራሲያዊ መንገድ ተንቀሳቅሶ አማራጩን ለህዝብ በማቅረብ የፖለቲካ ውድድር ማድረግ አለበት” የሚል እምነት እንዳላቸው አመላካች ነው፡፡
ይሄ የሚደገፍ ሃሳብ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር እነ ሌንጮ ለታም አሁን ያለውን ህግና ህገ መንግስት አክብረው ለመስራት ቢወስኑና መሻሻል ያለባቸውን ህጎችም በኋላ እያሻሻሉ ቢኬድ ጥሩ የፖለቲካ ለውጥ ይመጣል። እርግጥ ነው መታየት ያለባቸው አዋጆች አሉ፡፡ ለምሣሌ የሚዲያ፣ የሲቪክ ማህበራት፣ የምርጫ ቦርድ፣ የፀረ ሽብር አዋጆች አሉ፡፡ አሁን ደግሞ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አለ፡፡ እነዚህ አዋጆች እንዴት ለሁሉም ተስማሚ በሆነ ሁኔታ ይስተካከሉ የሚለውን መመካከር ያስፈልጋል። በውጭ ያሉ የፖለቲካ ሃይሎችም ለዚህ አይነቱ የእርቅና የመተባበር መንፈስ ዝግጁ ሆነው ከመጡ ጥሩ መሻሻልና ለውጥ ሊመጣ ይችላል። አሁን እነ አቶ ሌንጮ መምጣታቸው ጥሩ ምልክት ነው፡፡ በነገራችን ላይ አቶ ሌንጮ ዘመዴ ናቸው፤ ግን በፖለቲካ ምክንያት የተለያየን ነበርን፡፡ ተማሪዎች ሳለን እኔና ሌንጮ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ም/ቤት አባል ነበርን፡፡ አቋማቸውን አውቃለሁ፡፡ የኢትዮጵያ አርሶ አደሮች፣ ህዝቦች፣ ብሄር ብሄረሰቦች መብት እንዲከበርና በጋራ ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን እንፍጠር የሚል አመላከከት እንዳላቸው አውቃለሁ፡፡ ኦነግ ውስጥ ሆነውም ይሄን አመለካከት የለቀቁ አይመስለኝም፡፡
ዶ/ር ዲማ ነገኦም በሃገሪቱ ፖለቲካ ጥሩ ዕውቀት አላቸው፡፡ በዚህ መንገድ ሃገሪቱን ለማገልገል ከቻሉ ጥሩ ነው፡፡ በተመሳሳይ ከሌሎች የፖለቲካ ሃይሎችም ጋር ድርድርና ውይይት ማድረጉ ለሃገሪቱ ፖለቲካዊ መሻሻል ጠቃሚ ነው፡፡ ዶ/ር ዲማ ነገኦም ሆነ አቶ ሌንጮ ለታ በኦሮሞ ህዝብ ትግል ውስጥ ለረጅም ጊዜ የቆዩ ናቸው፡፡ የኢትዮጵያን ፖለቲካም በደንብ ያውቃሉ፡፡ መምጣታቸው በጣም ጠቃሚ ነው፡፡ እነሱም ሆነ ሌሎች የፖለቲካ ሃይሎች ወደ ሃገር ቤት መምጣታቸው ህዝብ አማራጭ እንዲያገኝ ያደርጋል። ከሁሉም በኩል የህዝብን መብት ማክበር ነው የሚጠበቀው፡፡


-----------



               “የፖለቲካውን ሂደት በጥንቃቄ ማየት ያስፈልጋል”
                  (ፕ/ር በየነ ጴጥሮስ፣ የመድረክ አመራር)

   በውጭ ሃገር ከሚገኙ ህዝባዊ መሠረት ካላቸው የፖለቲካ ሃይሎች ጋር የሚደረግ ማንኛውም ድርድር፣ ለዚህች ሃገር በጎ ውጤት ነው የሚያመጣው፡፡ አሁን ከኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ  ግንባር ጋር የተደረገው ድርድርና አመራሮቹም ወደ ሃገር ቤት መግባታቸው በአዎንታ የሚታይ ነው፡፡
ዞሮ ዞሮ የኛም ጥያቄና ትግል ከነበረው አንዱ እንዲህ ያለው ድርድር እንዲካሄድ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም ሽብርተኛ ካላቸው ቡድኖች ጋርም መነጋገሩ  መጥፎ ውጤት የለውም፡፡ መነጋገር ሁሌም በጎ ነው፡፡ የፀረ ሽብር አዋጁን ለጊዜው ወደ ጎን ትቶ፣ መነጋገሩ ለሃገሪቱ ፖለቲካ ይበጃል፡፡ ዋናው የድርድርና የንግግሩ መቋጫ፣ ነፃ ፍትሃዊ ምርጫ ማድረግ መቻል ነው፡፡ የመጨረሻው ውጤት ይሄ ነው፡፡ ይህ የሚፈለገው አይነት የፖለቲካ ሂደት እንዲመጣ ደግሞ መርጦ ከፈለጉት ጋር መደራደር ሣይሆን ከሁሉም ጋር መነጋገር ነው የሚያስፈልገው፡፡ መንግስት በውጭ ካሉ ሽብርተኛ ከተባሉት ጋርም ያለ አድልኦና ልዩነት መደራደር አለበት፡፡ ለኦነግ የተሠጠው እድል ለሌሎችም መሰጠት አለበት፡፡ አንዱን መርጦ አንዱን ማግለል ውጤቱ ጥሩ አይሆንም፡፡ ከዚህ በፊት የነበረው የሃገሪቱ የፖለቲካ ችግር፣ አንዱን መምረጥና ሌላውን ማግለል መሆኑ መታወቅ አለበት፡፡ አሁን የሽብር ፍረጃውን ወደ ጎን ትቶ መነጋገርን ማስቀደም፣ ለዚህች ሃገር ፖለቲካዊ መሻሻል ወሣኝ ነው፡፡ ከጥቂቶች ጋር ብቻ የሚደረግ ድርድር ግን የሃገሪቱን ሙሉ ችግር አይፈታም፡፡  አሁን ለድርድር አዲስ አበባ የገባው ድርጅት ከዚህ በፊትም ብዙ የድርድር ጥረት አድርጓል፡፡ ደብዳቤ ፅፎ ያውቃል፡፡ ለደብዳቤያቸው መልስ ያጡ የድርጅቱ መሪ፣ በራሳቸው ተነሳሽነት ሃገር ውስጥ እንደገቡም አይዘነጋም፡፡ በኋላም ታግተው፣ 24 ሰዓት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ሃገር ለቀህ ውጣ እንደተባሉ ይታወቃል፡፡ ስለዚህ ይህ ድርጅት ሃገር ውስጥ ለመግባት ከፍተኛ ጥረት ሲያደርግ ስለቆየ፣ አሁን ጉዳዩ ቀሎላቸው ሊገቡ ችለዋል፡፡ ያኔም ከሃገር ለቀህ ውጣ ከማለት ይልቅ መነጋገር ቢችሉ ኖሮ መልካም ነበር። ይህ ድርጀት ከእነሱ ይልቅ ለድርድሩ ብዙ ርቀት የተጓዘ ነው፡፡ በአንፃሩ ደግሞ በተካረረ ፅንፍ ላይ ያሉ ድርጅቶችም  አሉ፡፡ እነሱን ወደዚህ መድረክ ማምጣት ነው እንደ ትልቅ ውጤት ሊታይ የሚገባው፡፡ ስለዚህ መንግስት በዚህ ላይ ነው መስራት ያለበት፡፡አሁን ያለው የኢህአዴግ መንግስት ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩም በኢህአዴግ የተሰየሙ፣ ኢህአዴግ ናቸው፡፡ ስለዚህ የፖለቲካውን ሂደት በጥንቃቄ ማየት ያስፈልጋል፡፡ ለምርጫ ስርዓቱ መሻሻልና መዋቅራዊና አስተዳደራዊ ለውጥ ምን ያህል የተዘጋጀ ነው? የሚለው አጠያያቂ ነው፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ለውጡን በተግባር ማሳየት አለባቸው፡፡ በተለይ የፖለቲካው ወሳኝ ጉዳይ ምርጫ ነው፡፡ የምርጫው ሂደት ምን ያህል ሊቀየር ይችላል የሚለው ነው፣አሁን የሚያሳስበኝ፡፡ በዚህ እንቅስቃሴ ቆይተው፣ የህዝቡን ልብ ገዝተናል፣ እኛን ነው ህዝቡ የሚደግፈው ብለው ምርጫውን እንዳያበላሹት ስጋት አለኝ፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ የተረጋጋ ዲሞክራሲ እንዲመጣ ከተፈለገ ሥር ነቀል የምርጫ መዋቅራዊና  አስተዳደራዊ ለውጥ ያስፈልጋል፡፡ የሚደረጉ ድርድሮችም ይህን ታሳቢ ማድረግ አለባቸው፡፡ የምርጫ ሥርዓቱ ከተቀየረ ብዙ ፖለቲካዊ ለውጦች ልናይ እንችላለን፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደዚህ መንገድ የሚያደርሰንን ፍኖት ነው ማዘጋጀት ያለባቸው፡፡


--------


            “የህዝብ ድጋፍ ካላቸው ሃይሎች ጋር መደራደር ያስፈልጋል”
               (ዶ/ር መረራ ጉዲና፣ የኦፌኮና መድረክ አመራር)


   በቂ የህዝብ ድጋፍ ካላቸው ሃይሎች ጋር ነው በወሣኝነት መደራደር የሚያስፈልገው፡፡ ይህ አይነቱ ድርድር ለመጀመሩ እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ ከግንቦት 7፣ ከኦነግ፣ ከመድረክ፣ ከሠማያዊ ፓርቲና ከመሣሠሉት ህዝባዊ ድጋፍ ካላቸው ድርጅቶች ጋር እስካሁን ድርድር አልተጀመረም፡፡ የፖለቲካ መሻሻል ፍንጮች በበቂ መጠን ታይተዋል ሊባል የሚችለው ከእነዚህ ሃይሎች ጋር ድርድር ሲጀመር ነው፡፡ አሁን ወደ ሃገር ውስጥ የገቡት ሃይሎች ቀላል ቦታ ባይኖራቸውም ሌሎችም ቀሪዎች አሉ ለማለት ፈልጌ ነው፡፡
በነገራችን ላይ ሙሉ የፖለቲካ መሻሻል ፍንጮች እየታዩ ነው ለማለት፣ አሁን ኦዴግ ወደ ሃገር ውስጥ መግባቱ ብቻ በቂ አይደለም፡፡ በ1997 ህብረት ከኢህአዴግ ጋር ተደራድሮ፣ የጋራ ኮሚቴ ሁሉ አቋቁመን  ነበር፡፡ በኋላ ግን እነዚያን ነገሮች በሙሉ ውሃ ነው የበላቸው፡፡ ኢህአዴግ ድርድሮችን ጊዜና የተሻለ ነገር ሲያገኝ ደፍጥጧቸው ነው የሚያልፈው፡፡ አሁን በዋናነት ሁለት ነገሮች ወሣኝ ናቸው፡፡ አንደኛው በመሠረታዊ ጉዳዮች ላይ ስምምነት አለ ወይ? የሚለው ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ የተስማማንባቸው ነገሮች ስራ ላይ ይውላሉ ወይ? የሚለው ጥያቄ ነው፡፡ እርግጥ ነው አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ከአንደበቱ ጥሩ ጥሩ ነገሮች ይወጣሉ፡፡ ይህ ጥሩ ነው፡፡ በሌላ በኩል የተናገርከውን በስራ ፈፅም የሚል ግፊት አለ፡፡ በመጀመሪያ በጎ ንግግሮችን ማድረግ መልካም ነው፡፡ ከዚያ በኋላ ሃቀኛ ድርድር ማድረግ ነው፤ ቀጥሎም ስምምነት የተደረሠባቸውን ነገሮች ስራ ላይ ማዋል ነው፡፡ እነዚህ ሶስት ደረጃዎች ይጠበቃሉ፡፡ አሁን በመጀመሪያው ደረጃ ላይ ነው ያለነው፡፡ አሁን ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጎ በጎ ሃሳቦችን እየተናገሩ ነው  ያለው፡፡
በሌላ በኩል ለአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አስፈላጊ አይደለም፡፡ ፖለቲካዊ አጣብቂኝ ይፈጥርባቸዋል፡፡ ስለዚህ ይህን አንስተን ወደ ሁለተኛው ደረጃ፣ ወደ ሃቀኛ ድርድር መምጣት አለባቸው፡፡ የዚህ ሃገር ችግር የሚፈታው በኢህአዴግ ብቻ ሳይሆን ሌሎችም ተጨምረውበት ነው የሚለውን ኢህአዴግ ማመን አለበት፡፡ ይሄን ሲያምን ነው ሃቀኛ ድርድር ማድረግ የሚቻለው፡፡ ሰፊ ህዝባዊ መሠረት ካላቸው በሃገር ውስጥም በውጪም ከሚገኙ ድርጅቶች ጋር መስራት የሚችለውም ይሄን አምኖ ሲቀበል ብቻ ነው። አሁን ከኦዴግ ጋር የተደረገው ድርድር መልካምነቱ እንዳለ ሆኖ ማለቴ ነው፡፡
አሁን በስፋት እየታየ ያለው በገዥው ፓርቲ በኩል የገፅታ ግንባታ ዘመቻ ነው፡፡ በዚህ ነው ተጠምደው ያሉት፡፡ እኔ እንኳ ከእስር ከተፈታሁ በኋላ የምሁራን ውይይት እየተባለ አራት ያህል ውይይቶች ላይ ተሳትፌያለሁ፡፡ እስካሁን በተጨበጠ መንገድ የሃገሪቱ ችግሮች ምን ነበሩ? ከምን ተነሱ? ለምን ድንጋይ ተወረወረ? ለምን ፖለቲከኞች ተሰደው ሌላ አማራጭ ያዙ? የሚሉ ጥያቄዎችን ለመፈተሽ የደፈረ መድረክ ግን አላጋጠመኝም፡፡ በየመድረኩ እየታዩ ያሉት 95 በመቶ ያህል በሃገሪቱ ቀውስ ውስጥ ምንም ተሣትፎ የሌላቸው ናቸው፡፡
በእነዚህ ስብሰባዎች ጥያቄ አንግበው የመብት ትግሉን ሲገፉ ከነበሩት ወገኖች  ድምፅ አይሰማም፡፡ ይሄ ለኔ ይገርመኛል፡፡ ሃገር ግንባታ ይባላል ግን የቀውሱን ምንጭ ማንም ለመፈተሽ የሚፈልግ  አይታይም፡፡ ማሳተፍ ያለበትን ያሣተፈ መድረክ አላጋጠመኝም፡፡ ለአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር በጎ ከመመኘት በስተቀር በዚህ በኩል ያለው ጉድለት ለኔ ያሰጋኛል፡፡ ጠ/ሚኒስትሩ የኢህአዴግ ካድሬዎችንና መሪዎችን ወደ ለውጥ ካልመሩ አስቸጋሪ ነው፡፡ በውጭ ያሉ የፖለቲካ ሃይሎች፣ ይህ ሳይለወጥ ቢመጡ ከማማረር በቀር ፋይዳ አይኖረውም፡፡ እነዚህ ተፈትሸው ሲታከሙ ነው ሃቀኛ ድርድር የሚደረገው፡፡
ሃቀኛ ድርድር ማለት ሰጥቶ መቀበል ነው፡፡ ሰጥቶ መቀበል ደግሞ ከላይ ዝም ብሎ የሚጫን ሣይሆን የህዝቦችን ጥቅም ማስቀደም ማለት ነው፡፡ እስካሁን ለኢትዮጵያ ምን አይነት ምርጫ ማካሄድ ያስፈልጋል? የሚለው አልተነሳም፡፡ ህገ መንግስቱ ነው አንዱ ጣጣ የፈጠረው፡፡ “ሕገ መንግስቱ የኢትዮጵያ ህዝብ የወሰነው ነው የሚለው ትክክል አይደለም” ብለዋል የቀድሞ ፕሬዚዳንት፡፡ ስለዚህ ህዝባዊ ውሣኔ ያስፈልጋል ማለት ነው፡፡ ለኔ ያለፉት 27 ዓመታት የኢህአዴግ ሙከራ ታላቅ መከራ ሆኖ፣ ወደ ታላቅ ክሽፈት ያመራ ነው፡፡
ስለዚህ አሁን ከታላቅ ክሽፈት ወደ ታላቅ ሙከራና ውጤት ነው ልንሄድ የሚገባው ማለት ነው፡፡ ኢህአዴግ እነማን ሠፊ ህዝባዊ መሠረት እንዳላቸው ያውቃል፡፡ በውጭም በሃገር ውስጥም እነማን ህዝብ እንደሚከተላቸው ኢህአዴግ ጠንቅቆ ያውቃል፡፡ ስለዚህ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አንደበታቸው በጎ ማመንጨቱ እንዳለ ሆኖ፣ አሁን ወደ ሁለተኛው ደረጃ ተሸጋግረው፣ ያለ ገደብ ከፖለቲካ ኃይሎች ጋር መነጋገር ያስፈልጋል፡፡
እኔ ከእስር ቤት ከወጣሁ በኋላ በዚህ ሃገር የፖለቲካ ሂደት፣ ጥንቃቄ የተሞላበት ተስፋ ነው የማደርገው። በ1966 የተሻለ ዕድል አምልጦናል፣ በ1983 ዕድል አምልጦናል፣ በ1997 ጥሩ አጋጣሚ አምልጦናል። አሁንም ዕድል ከፊታችን ተቀምጧል፡፡ ይሄኛው የለውጥ ዕድል ሊያመልጠን አይገባም፡፡ ስለዚህ ሁሉም በጥንቃቄ ነው ሊያየው የሚገባው፡፡ የተጀመረው ጥሩ አንደበትና ንግግር ተስፋ እንድናሳድር አድርጎናል፤ግን በከፍተኛ ጥንቃቄ ነው ተስፋ የምናደርገው፡፡


-------------


               “ያልተለመደ ነገር እንዲመጣ ነው መስራት ያለብን”
                 (ዶ/ር ጫኔ ከበደ፣ የኢዴፓ ሊቀ መንበር)

   ጠቅላይ ሚኒስትሩ የመጀመሪያ ደረጃ ሊባሉ የሚችሉ፣ በጎ እርምጃዎችን እየወሰዱ ነው ማለት ይቻላል። በአንደበታቸው ትኩሳቱን ለማብረድ ሞክረዋል፡፡ ከዚያም አልፎ ህዝቡ ከተስፋ መቁረጥ ወደ ተስፋና ቀናውን ወደ መመልከት እንዲሸጋገር አድርገዋል፡፡ ወደ ተግባር እስኪቀየር አሁን የሚናገሯቸው ነገሮች ጥሩ ነገር እየፈጠሩ ነው፡፡ የዲሞክራሲ ስርአት ግንባታው ከፍረጃና ከጥላቻ ወጥቶ በትክክለኛው አቅጣጫ እንዲመራ ጥረት እያደረጉ መሆናቸው በበጎ የሚታይ ነው፡፡ ይህ ሃሳባቸው ለተቃውሞው ጎራ እፎይታን የሰጠ ነው፡፡ ለተወሰኑትም እርካታን የፈጠረ ሆኖ አይተነዋል፡፡ እሳቸው አሁን የያዙት አቋም በሃገር ውስጥም በውጪም ያሉ ፖለቲከኞች በድርድር ውስጥ መካተት እንዳለባቸው ነው፡፡ ይሄ ድርድር በውይይት የምንፈልጋትን ኢትዮጵያ ለማምጣት እንደሚቻል፣ ፍንጭ የሰጠ በጎ ሃሳባቸው ነው፡፡
የተረጋጋ ፖለቲካ ለማካሄድ ውይይት ማድረግ እንደሚገባ ደጋግመው ተናግረዋል፡፡ ይሄ ደግሞ በተቃውሞ ጎራ ያለነው ሰዎችም ሃሳብ ነው፡፡ ሃሳቡ የጋራችን ከሆነ ተቀራርቦ ተነጋግሮ፣ ለዚህች ሃገር የሚሆን መፍትሄ ለማግኘት ምን ይቸግረናል? ለወደፊት በጎ ሃሳባቸውና ንግግራቸው ወደ ተግባር እንዴት እንደሚቀየር ማየት የሚገባን ይሆናል፡፡
በውጭ ላሉ የፖለቲካ ሃይሎች ጥሪ አቅርበው ነበር። አሁን ውጤት እያመጣ ይመስላል፡፡ እነ አቶ ሌንጮ ለታም በዚህ ተነሳስተው እንደመጡ መገመት ይቻላል። ይሄ ጥሩ የፖለቲካ ጅምር ነው፡፡ ጅምሩ ለሌሎችም ሊደርስ ይገባል፡፡ ወደ ሃገር ውስጥ ገብተው፣ ለሃገራቸው ያላቸው ሃሳብ ተደምጦ፣ ለዚህች ሃገር ወሣኝ የሆነ ጠቃሚ ምዕራፍ የሚጀመርበት ሁኔታ መፈጠር አለበት፡፡ ፖለቲካውን በዚህ መንገድ ማሳደግ የምንችልበት ዕድል አለ፡፡ ቀጥሎ ብሄራዊ መግባባት መፈጠር አለበት፡፡ ለብሄራዊ መግባባት ደግሞ አሁን ያለው ጅምር ቀና  መንገድ ይመስላል፡፡ የኛም ግፊት ይህ ሂደት ሰፍቶ በዓለማቀፍ ደረጃ የሚታይ ድርድር እንዲካሄድ ነው የምንፈልገው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እስካሁን የሚያደርጓቸው ንግግሮች፣ የመቻቻል ፖለቲካ በዚህች ሃገር እውን ማድረግ የሚያስችል ነው፡፡ ከዚህ አንፃር በኛ በኩል ጥሩ ስሜት ነው ያለን። በአጭር ጊዜ ውስጥ ደግሞ ወደ ተግባር ቢቀየር፣ የበለጠ ጥሩ ነገር ይፈጥራል፡፡
ኦዴግ ብቻ ሳይሆን በርካታ የፖለቲካ ሃይሎችና ፖለቲከኞች በፍረጃና በጥላቻ ፖለቲካ ተገፍተው ከሃገር ውጪ አሉ፡፡ እነዚህ ሁሉ ያለ አድልኦ መጥተው፣ ፖለቲካው የሚስተካከልበት ሁኔታ መፈጠር አለበት። የፖለቲካ ሜዳውን አንድ እርምጃ ለማስፋትና ከ2 አመት በኋላ ለሚደረገው ምርጫ ውጤታማነት፣ ሁላችንም በመቻቻል የፖለቲካ መንፈስ መንቀሳቀስ መቻል አለብን፡፡
በውጭ ሃገር ያሉ ተቃዋሚ ሃይሎችን በአጠቃላይ ወደ ድርድር ለማምጣት ደግሞ ዋስትና መስጠት ያስፈልጋል፡፡ የታገዱበትን ህግ ማንሳት ይገባል፡፡ ሁሉም ሃይሎች ሃገር ውስጥ ገብተው እንዲደራደሩ ከተፈለገ፣ ስጋቶችን በመሉ ማስወገድ ያስፈልጋል፡፡ በዓለማቀፍ ደረጃ ገለልተኛ የሆኑ ሰዎች እንዲያደራድሯቸው ማድረግም ያስፈልጋል፡፡ መንግስት በዚህ ላይ ትኩረት ሰጥቶ ቢሠራ መልካም ነው፡፡ በቅድመ ሁኔታ ላይ የታጠረ ድርድር አያስፈልግም፡፡ ዞሮ ዞሮ የድርድር ውጤት ነፃ፣ ተዓማኒና ፍትሃዊ ምርጫ የሚካሄድበት መንገድ መፍጠር ነው፡፡ መልካም ፖለቲካዊ ሂደት ውጤቱ ይሄው ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ያልተለመደ ነገር እንዲመጣ ነው መሥራት ያለብን፡፡ አሁን ምክንያታዊ ፖለቲካ ነው የሚያስፈልገን፡፡ መንግስት ለዚህ አይነቱ ፖለቲካ ሁሉም የሚሳተፍበት ሜዳ ማመቻቸት አለበት፡፡


------------------


               “ጠ/ሚኒስትሩ የመግባባት ፖለቲካ እንዲሰፍን ሙከራ እያደረጉ ነው”
                  (ዶ/ር በዛብህ ደምሴ፣ የመኢአድ ፕሬዚዳንት)


   ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚያነሷቸው ሀሳቦች ለሃገራዊ መግባባት ጠቃሚ ናቸው፡፡ ብዙ ፖለቲከኞችም በበጎ የሚመለከቱት እንደሆነ በግልጽ እያየን ነው፡፡ በውጭ ሃገርም ካሉ ጋር ድርድር ያስፈልጋል እያልን በተደጋጋሚ ስንነጋገር ነበር፡፡ እሳቸው አሁን ይህን ተቀብለው ጥሪ ከማቅረብ ጀምሮ ተግባራዊ እርምጃዎችንም እየወሰዱ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሃገር ውስጥም ሆነ በውጭ ካሉ ፖለቲከኞች ጋር ለመነጋገር ቀና መሆናቸውን በተግባርም ጭምር እያመለከቱ ነው፡፡ የመግባባት ፖለቲካ በሃገሪቱ እንዲሰፍን ሙከራ እያደረጉ ይመስለኛል፡፡
ቀደም ሲል እኛም የተሣተፍንበት የብሄራዊ መግባባት ጉባኤ በአሜሪካ ዋሽንግተን ተካሂዶ ነበር። በስብሰባው በውጭ የሚገኙ ሁሉም የፖለቲካ ድርጅቶች ተገኝተው ነበር፡፡ ከ26 በላይ ናቸው፡፡ እኔ እንደተረዳሁት፣ አብዛኞቹ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግሮችና እርምጃዎች ተስፋ ሰንቀዋል፡፡ እኛም በዚሁ የብሄራዊ መግባባት ጉዳይ ላይ ከፕሬዚዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ ጋር በቅርበት ተነጋግረን፣አዎንታዊ ምላሽ አግኝተናል፡፡ ቀናነት እንዳለም ተገንዝበናል፡፡ ፖለቲካውን ከመፈራረጅና ከጥላቻ የፀዳ ለማድረግ፣ በመንግስት በኩል ፍላጎት እንዳለ መገንዘብ ችለናል። ጠ/ሚኒስትሩ ለኢትዮጵያ አንድነት አስፈላጊ የሆኑ ሃሣቦች እያፈለቁ ነው፡፡ ይህን በበጎ መልኩ ነው የምናየው፡፡
ላለፉት 27 ዓመታት ስንታገል የነበረው ለኢትዮጵያ አንድነት እንደመሆኑ፣ ይህን የሚደግፍ  ሃሣብ ሲመጣ የምንቃረንበት ምክንያት የለም፡፡ የኢትዮጵያዊነት አንድነት ጥቅሞችን ጠቅላይ ሚኒስትሩ መስበካቸው፣ በበጎ የምንመለከተው ነው፡፡ ለኢትዮጵያ አንድነት የሚታገሉ፣ ነገር ግን በትጥቅ ትግል ውስጥ ያሉ የፖለቲካ ሃይሎችንም፣ ልክ እንደ እነ ሌንጮ ለታ በማግባባት፣ ወደ ሃገር ውስጥ ገብተው፣ የፖለቲካው ተዋናይ እንዲሆኑ መፍቀድ አለባቸው፡፡ አሁን ከእነ ሌንጮ ለታ ጋር የሚደረገው ድርድር፣ ለቀሪና ለሰፊው ድርድር በር ከፋች ይሆናል የሚል ተስፋ አለኝ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስለ አንድነት፣ ስለ ኢትዮጵያዊነት የሚናገሩትን በእጅጉ እደግፋለሁ፡፡ ጅማሮአቸው ጥሩ ነው፡፡ በዚሁ የፖለቲካ ለውጥ ቀጥለው፣ሁላችንም አንድ ቦታ ላይ ብንገናኝ ጥሩ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ችግር ሊፈታ የሚችለው በሃገራችን ዲሞክራሲ ሲዳብርና ፖለቲከኞች ተቀራርበው ሲሰሩ ብቻ ነው፡፡ አሁን ያለው ሁኔታ ለመነጋገርና ለመወያየት አመቺ ይመስላል፡፡


No comments:

Post a Comment