Pages

Tuesday, May 22, 2018

የኢትዮጵያ ፌዴራሊዝም ከቋንቋ ወደ ግዛታዊነት ቢሸጋገርስ?


`በክንፈ ኪሩቤል
በክፍል አንድ ሕገ መንግሥቱ ስለብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች፣ መብቶችና የፌዴራሊዝሙን ሕገ መንግሥታዊ ትርጉምና ችግሮች ተመልክተናል፡፡ በክፍል ሁለት ደግሞ በኢትዮጵያ የቋንቋ ፌዴራሊዝም መተግበር ከተጀመረ ወዲህ የታዩትን ችግሮች ተመልክተናል፡፡ በክፍል ሦስት ምን ማድረግ ይገባናል የሚል ሐሳብ እንዳስሳለን፡፡

ኢትዮጵያ አገራችን ባለፉት ወራት አንዣቦባት የነበረውን የጥፋትና የዕልቂት ድግስ ፈጣሪ እግዚአብሔር በቸርነቱና በይቅርታው በማስቆም፣ ፊሪኃ እግዚአብሔር ያላቸውንና ስለሕዝብ የሚያስቡትን ዓብይ አህመድን (ዶ/ር) መጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም. ጠቅላይ ሚኒስትር አድርጎ በሥልጣን ወንበር ላይ አስቀምጧል፡፡ ሕዝባችንም ከእኚህ ወጣትና ማስተዋል ከሚታይባቸው መሪያችን ጎን በመሆን በሚደረገው ሰላማዊ ትግል እንዲሳተፍ፣ ዘብም እንዲቆም ጸሐፊው ያሳስባል፡፡
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ ሚያዝያ 18 ቀን 2010 ዓ.ም. በደቡብ ክልላዊ መንግሥት ዋና ከተማ ሐዋሳ ስታዲዮም ተገኝተው ለሕዝብ ንግግር ካደረጉ በኋላ፣ በምክር ቤት አዳራሽ ተገኝተው ታሪካዊ ውይይት ከሕዝብ ተወካዮች ጋር አካሂደዋል፡፡ የሕዝብ ተወካዮች ላቀረቡላቸው በርካታ ጥያቄዎቸና ብዙ ጉዳዮች በግልጽና ቀላል በሆነ አገላለጽ አስረድተዋል፡፡
ዶ/ር ዓብይም የደቡብ ክልልን በንግግራቸው ‹‹ትንሿ ኢትዮጵያ›› ብለውታል፡፡ ለምን? ምሳሌነቱ ታላቅ ስለሆነ፡፡ እነዚህ ሕዝቦች የቀደምትም ሆነ የአሁኑ ኢትዮጵያዊነት ምሳሌ ናቸውና፡፡ ምክንያቱም የሕዝባችንን የቀድሞ መንግሥታት ታሪክ የደገሙት ስለሆነ፡፡ ሕገ መንግሥታችን በአንቀጽ 39 ንዑስ አንቀጽ 5 ከደነገገው በተቃራኒ የደቡብ ክልል ሕዝቦቻችን ያስመሰከሩት፣ ‹‹የአንተ ሕዝብ ከእኛ ሕዝብ የሚያመሳስለው የጋራ ፀባይ የሚያንፀባርቅ ባህል ወይም ተመሳሳይ ልምዶች የለውም፣ እንዲሁም ልንግባባበት የሚያስችለን የጋራ ቋንቋ የለንም፣ የጋራችን የሆነና ወይም ከእኛ ጋር የምትዛመድበት ህልውናና የሥነ ልቦና ትስስር የለህምና ተለያይተን መኖር አለብን፤›› አላሉምና፡፡ ከሃያ ሚሊዮን ያላነሰ ሕዝብ በሚኖርበትና 56 ቋንቋዎች በሚነገርበት ክልል ጎሳንና ቋንቋን መሠረት ያላደረገ ግዛታዊ የፌዴራሊዝም መንግሥት ይሏል ይኼ ነው፡፡  
እነሆ በ23 ዓመታት ታሪክ ውስጥ ዶ/ር ዓብይ አንድ ዋና የተዘጋ በርን ሊከፍቱ ነው፡፡ እስከምናውቀው በአገራችን ታሪክ በዘውዳዊም ሆነ በወታደራዊ ደርግ መንግሥታት፣ እንዲሁም ባለፉት 27 የኢሕአዴግ አገዛዝ ዘመናትም ጭምር ሕገ መንግሥታችንን እንደ ፍፁማዊ ሕግ አድርገን ስናይ ቆይተናል፡፡ በሕገ መንግሥቱ ላይ መጨመር መቀነስ ወይም ማሻሻል ያስፈልጋል የሚል ቃል ከኢሕአዴግ ሰምተንም አናውቅም፡፡ ይህ ከኢሕአዴግ ሲመጣ መልካም ዜና ነው፡፡
የኢትዮጵያ መንግሥት የመሪነትን የሥልጣን ዘመን ገደብ በተመለከተ ሕገ መንግሥቱን በማሻሻል የመሪውን የሥልጣን ዘመን ከሁለት ጊዜ በላይ እንዳይበልጥ መገደቡ መልካም ነው፡፡ በሌሎች የአፍሪካ አገሮች እንደምንመለከተው የአገር መሪዎች ሕገ መንግሥትን ለማሻሻል የሚፈልጉበት ዋና ምክንያት የአገዛዝ ዘመናቸውን ለማራዘም እንጂ፣ ለመገደብ አይደለም (እነ ቡሩንዲ፣ ኮንጎ፣ ብራዛቪል፣ ኡጋንዳ ወዘተ)፡፡
በሐዋሳ በተደረገው ውይይት ሌላ አንድ ዓብይ ጉዳይ ተነስቷል፡፡ ‹‹የብሔርተኝነት›› ጉዳይ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትራችን በሚገርም ሁኔታ በሚያስተምርና በሚያሳምን መንገድ አስረድተዋል፡፡ ከ50 ዓመታት በፊት ‹‹የብሔርተኝነት›› ጉዳይ ስለመነሳቱ፣ ይኼም ጉዳይ ከጣራ በላይ መራገቡንና ‹‹የብሔርተኝነት›› ጉዳይ ባስከተለው ትግል ምክንያት የታሰሩ፣ የሞቱና የተሰደዱ ብዙዎች እንደነበሩ ከገለጹ በኋላ ዛሬ ሲዳማነት፣ ወላይታነት፣ ጌዴኦነት፣ ወዘተ መሆን መልካም ቢሆንም ከሁሉ በላይ የሚበልጠው ግን በአንድነት ኢትዮጵያዊ መሆን ነው ባሉበት ወቅት፣ በስብሰባው አዳራሽ የነበረው ጭብጨባ ያመላከተው ሕዝባችን ምን ያህል ጎሰኝነትንና ጎጠኛነትን እንደ ጠላ ነው፡፡ ይህንን መሰል የሕዝብ ስሜት በመቐለ፣ በጎንደር፣ በባህር ዳር፣ በጅግጅጋ፣ በአምቦ ዶ/ር ዓብይ በተገኙበት የሕዝብ ስብሰባ ወቅት በገሀድ ታይቷል፡፡    
በዚሁ አጋጣሚ በሕገ መንግሥታችን ውስጥ መሻሻል የሚገባቸው በርካታ አንቀጾች እንዳሉ የኢትዮጵያ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ክቡር ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ከአሜሪካ ድምፅ ራዲዮ ጣቢያ ጋዜጠኛ ጋር ሚያዝያ 21 እና 23 ቀን 2010 ዓ.ም ባደረጉት ቃለ መጠይቅ ተናግረዋል፡፡ በነገራችን ላይ ዶ/ር ነጋሶ የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት አርቃቂ ኮሚሽን ሊቀመንበር ነበሩ፡፡ ስለዶ/ር ነጋሶ ማንነት በርካታው የኢትዮጵያ ሕዝብ ሊያውቅ ስለሚችል ስለእሳቸው ተጨማሪ መግለጽ አስፈላጊ አይሆንም፡፡ በእርሳቸው መሪነት የተቀረፀው ‹‹የቋንቋ›› እና ‹‹የመገንጠል›› መብትን ያዘለው አንቀጽ 39 ያስከተላቸው ብዙ ውስብስብ ችግሮችንና ቀውሶችን ዛሬ ላይ ሆነው ሲያዩት ምን እንደሚሰማቸው በትክክል መገመት ባይቻልም፣ ከአሜሪካ ድምፅ ሬዲዮ ጋዜጠኛ ጋር ያደረጉትን ቃለ ምልልስ ላዳመጠ ሰው ‹‹ኢትዮጵያዊነት›› መልካም መሆኑን አምነው፣ ‹‹የብሔር ብሔረሰብ›› መብቶችን እንዳይጫን የሚል አንደምታ ያለው መልስ ሰጥተዋል፡፡
ዶ/ር ነጋሶ እንደሚያስታውሱት በእሳቸው መሪነት የተረቀቀው ‹‹የአዋጆች ሁሉ አዋጅ›› የሆነው ሕገ መንግሥታችን የአገራችንን መፃዒ ዕድል የራስን ዕድል በራስ የመወሰን እስከ መገንጠል ጉዳይን የመሰለ ነገር ሲያስቀምጥ፣ ‹‹የብሔርና የብሔረሰብ የሕዝቦች›› ትርጉም አልሰጠም፡፡ ሰማንያ አምስት ቋንቋዎች ይነገሩባታል በምንላት አገራችን በሕገ መንግሥታችን ውስጥ አንዱን ሕዝብ ‹‹ብሔር››፣ ሌላውን ‹‹ብሔረሰብ››፣ ሌላውን ‹‹ሕዝብ›› ሊያሰኙ የሚችሉ ሳይንሳዊ፣ ታሪካዊ፣ ሕጋዊም የሆኑ አንዳችም ማስረጃዎች፣ እንዲሁም መሥፈርቶቹ አልተጠቀሱም፡፡ ሕዝባችን ‹‹ብሔር››፣ ‹‹ብሔረሰብ››፣ እና ‹‹ሕዝብ›› በመባሉ የሚያገኘው የተለየ ጥቅምና መብት የለውም፡፡ ስለቋንቋም ቢሆን የመጠቀም መብቱ በመጀመርያ የተሰጠው ከፈጣሪው (ከእግዚአብሔርና ከወላጁ) እንጂ፣ በየትኛውም ሕገ መንግሥት የሚሰጥ መብት አይደለም፡፡ ሕገ መንግሥት ሳይኖር ሕዝቦች በቋንቋዎቻቸው ተጠቅመዋል፡፡ ማንም ይህንን መብታቸውን ሊቸራቸው ወይም ሊነጥቃቸው አይችልም፡፡ ቋንቋ የሚጠፋው የቋንቋው ተናጋሪ ትውልድ ከጠፋ ብቻ ነውና፡፡
የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እየተባለ 23 ዓመታት ብናሳልፍም፣ ይህ አጠራር ምን ለማለት እንደሆነ ለብዙዎች ግልጽ አይደለም፡፡ ከሃምሳ ስድስቱ የደቡብ ሕዝቦች/ቋንቋዎች/ጎሳዎች ‹‹ብሔር›› ማን እንደሆነ፣ ‹‹ብሔረሰብ›› ማን እንደሆነ፣ ‹‹ሕዝብ›› ማን እንደሆነ የሚታወቅ ነገር የለም፣ ብናውቅ መልካም ነበር፡፡ እነዚህ ሕዝቦች በአኗኗራቸውና በኢኮኖሚ ዕድገታቸው የተራራቀ ልዩነት ኖሯቸው ዓናይም፣ ከኋላ ቀር ግብርና የዘለለ ኢኮኖሚ የላቸውም፡፡ የቋንቋ ተናጋሪዎቻቸው ብዛት ሊለያያቸው ይችል ይሆናል እንጂ፣ አንዱን ሕዝብ ‹‹ብሔር››፣ ሌላውን ‹‹ብሔረሰብ›› እና ‹‹ሕዝብ›› ብሎ ለመናገር ምንም ተጨባጭ ሳይንሳዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ወይም ታሪካዊ መሥፈርት ስለሌለ ቃላቱ እምብዛም ትርጉም አይሰጡም፡፡ ለምሳሌ ከ23 ዓመታት በኋላም የሲዳማን፣ የወላይታን፣ የኮንሶን፣ የጌዴኦን፣ የጉራጌን፣ የሐዲያን፣ የከፊቾን፣ የአማሮን፣ የቡርጂን፣ የቤንችን፣ የማጂን፣ የሸኪቾን፣ ወዘተ ሕዝቦች በ‹‹ብሔር››፣ በ‹‹ብሔረሰብ›› እና በ‹‹ሕዝብ›› በሳይንሳዊ አመክንዮ መድቦ ማሳየት የደፈረ የለም፡፡ ዶ/ር ነጋሶ ይህንን ጉዳይ አሁን በጥሞና የተገነዘቡት ይመስላል፡፡ ዶ/ር ነጋሶ የአገራችን ፕሬዚዳንት ሆነው በቆዩባቸውና በኢሕአዴግ ውስጥ በነበሩባቸው ዓመታት የገጠሟቸውን ችግሮች ወደ ዳር ትተን፣ የሕገ መንግሥታችንን መሻሻል ተገቢነት አምነው ‹‹ከተፈለገ የማይቻል ነገር የለም›› ብለው ለቪኦኤ ሬዲዮ ጋዜጠኛ መናገራቸው፣ ከሕገ መንግሥታችን የአርቃቂ ኮሚሽን መሪ አንደበት ሲወጣ ትልቅ ምስክርነት ነው፡፡ የብሔርተኝነትን ጉዳይ አሁንም ለማራገብ የሚፈልጉ ወገኖች ስላሉ እስኪ ቆም ብለው በእውነት ራሳቸውን ይጠይቁ፡፡ ማን ነበር ከዚህ ሥርዓት ተጠቃሚ? በአገሪቱስ የተፈጠረው የገዥ መደብ ማንን ይወክላል? ባለንበት በአሁኑ ወቅት ከግል ጥቅማችን ባሻገር የሕዝብን ጥቅም ማስቀደም መልካምነት ነው፡፡ መልካም ከማድረግ የበለጠ መልካም ነገር የለም፡፡
እንግዲህ ልብ ብለን ከተመለከትን ዶ/ር ዓብይ አህመድ ሐዋሳ ላይ ሲናገሩ፣ ‹‹ሲዳማነት፣ ወላይታነት፣ ጌዴኦነት፣ . . . ወዘተ መሆን መልካም ቢሆንም፣ ከሁሉ በላይ የሚበልጠው ግን በአንድነት ኢትዮጵያዊ መሆን ነው፤›› ያሉበት ምክንያት ለሁላችንም ግልጽ ሊሆን ይገባል፡፡ ስለእውነት እንናገር ከተባለ ከደቡብ ሕዝቦች የምንማረው ሀቅ የኢትዮጵያን መበታተን ሲተነብዩ ለኖሩት ሁሉ ምላሽ የሰጠና ዝም ያሰኘ፣ ኢትዮጵያ እንደ ቀድሞው ዘመናት ችግሮቿን በሕዝቦቿ መፍትሔ እየሰጠች መኖር እንደምትችል ያረጋገጠልን በመሆኑ ነው፡፡
የሕገ መንግሥታችንን የማሻሻሉ ጉዳይ ከተነሳ አይቀር ባለፉት 23 ዓመታት በርካታ የአገራችን የሕግ ሰዎች፣ ምሁራን፣ የታሪክ አዋቂዎችና የአገር ሽማግሌዎች፣ . . . ወዘተ ሲያነሱት የነበረ ሲሆን፣ ያሉትን ሐሳቦች በማካተት በሕገ መንግሥታችን ውስጥ ሊሻሻል የሚገባቸውን፣ አንድነታችንን እንዲሸረሽር ያደረገውን የአንቀጽ 39 ጉዳይ በጥንቃቄ እንዲታይ የሚደረግበትን መንገድ ዶ/ር ዓብይ አህመድ እንዲያመቻቹ ጸሐፊው በአክብሮት ይጠይቃል፡፡
የቅድመ ሁኔታዎች መሟላት
ሆኖም የአንዳንድ ቅድመ ሁኔታዎች መሟላት የግድ ይላል፡፡ ባለፉት 27 ዓመታት የደረሰብን ተፅዕኖ ቀላል አልነበረም፣ አይደለም፡፡ ባለፉት መንግሥታት የዴሞክራሲ ባህላችን እንዲጎለብት ባለመደረጉ የተነሳ ለአገር የሚበጁ ምክሮች ሲቀርቡ፣ ስህተትን ለማረም ሐሳብ ሲሰጥ በበጎ ዓይን ከማየትና እስኪ እናጢነው ከማለት ይልቅ ሐሳብ አቅራቢውን እንደ ጠላት መፈረጅ፣ ማኩረፍ፣ ስሙን ማጉደፍ፣ ማስፈራራትና ማሳደድ የመሳሰሉትን ስንመለከት ኖረናል፡፡ ይህ ሊቆም ይገባል፡፡ የወዳጅ ምክር በጎ ነው፣ የጠላትም ምክር ደግሞ ክፉ ነው፡፡ ስለሆነም ለአገራችንና ለመንግሥታችን መልካም ምክርን የሚለግሱንን ሰዎችን በጥሞና ማዳመጥ ይገባል፡፡ የውጭ ርዕዮተ ዓለም ‹‹እንደ ወረደ›› እየገለበጥን ያተረፍነው ጥፋትን ብቻ ነው፡፡
ላለፉት 23 ዓመታት ቋንቋን መሠረት ባደረገው ፌዴራላዊ አከላለል የተነሳ የሕዝባችን ሥነ ልቦና ወደ ጎሳዊ አስተሳሰብ በእጅጉ አዘንብሏል፡፡ ከዚህ አስተሳሰብ ለመውጣት ግን ጊዜን፣ ጥረትን፣ ትዕግሥትን፣ መደማመጥንና ሰፊ ሕዝባዊ ውይይትን ማካሄድ ይጠይቃል፡፡ አንድ ትውልድ በዚህ ዘመን ተፈጥሯልና፡፡ ቀድሞ ያልነበረ የጎሰኝነት ሥነ ልቦና ተፈጥሯል፣ ክልላዊ አስተሳሰብ ሰፍኗል፣ ብዙ ውስብስብ ችግሮች ተፈጥረዋል፣ በአንድ ጀንበር ብርሃን የሚፈታ ነገር የለም፡፡ ሆኖም ኢትዮጵያውያን ለገራቸው ችግሮች የሚበጃቸውን መፍትሔ ከራሳቸው በማፍለቅና በራሳቸው አስተሳሰብ  በመመራት፣ ለችግሮቻቸው ሁሉ እንደ  ጊዜው ሁኔታ መፍትሔ በማግኘት የሚታወቁ ናቸው፡፡
ይህንን ሥራ ለማገዝ የሚችል አጋዥ መዋቅር ማስፈለጉ አይቀርም፡፡ ይህም መዋቅር ብሔራዊ የአማካሪ ሸንጎ ተብሎ ሊሰየም ይችላል፡፡ የሸንጎ አባላቱም ከመላው አገሪቱ የተውጣጡ አባ ገዳዎች፣ ኡጋዞች፣ ሡልጣኖች፣ መንፈሳዊ አባቶች፣ የጎሳ መሪዎች፣ ታዋቂ ሽማግሌዎች፣ ሴቶች፣ የሕግ ሰዎች፣ የታሪክ አዋቂዎችና የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች፣ . . . ወዘተ ሊያካትት ይችላል፡፡ የዚህ ሸንጎ ዓላማ ሕዝባችንን ከጎሳ አስተሳሰብ ወደ አገራዊ አንድነት የሚያመጣውን መንገድ እንዲጠርግና እንዲረዳ ነው፡፡ ፌዴራሊዝሙን ከማሻሻል በፊት የሕዝቡ አስተያየት ማድመጥና ማካተት የግድ ነው፡፡ ድንበሮች እንዴት ይካለሉ? ከጥንቶቹ ግዛቶች ተጨማሪ ስንት ይጨመራሉ? ወዘተ የመሳሰሉትን ሰፊና ግልጽ ውይይት ሊደረግበት ይገባል፡፡ ሸንጎው ከፖለቲካ ድርጅቶች ተፅዕኖ ውጪ መሆን ይኖርበታል፡፡ እናም ኢትዮጵያዊ መፍትሔ ከዚህ ይመነጫል፡፡
አሁን ያለውን ቋንቋን መሠረት ያደረገን ፌዴራላዊ አከላለል ወደ ግዛታዊ ፌዴራላዊ አወቃቀር መቀየር መልካም ይሆናል፡፡ ‹‹ትንሿ ኢትዮጵያ›› በማለት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ የጠሩትና ሃምሳ ስድስት ቋንቋዎች የሚነገሩበት የደቡብ ሕዝቦች አማርኛን እንደ ሥራ ቋንቋ በመጠቀም በአንድነት የመኖራቸው ጉዳይ እንደ ግዛታዊ ፌዴራሊዝም ተሞክሮ በመላው ኢትዮጵያ ሊተገበር የሚገባ ነው፡፡ ቋንቋ ከመግባቢያነት መሣሪያነት ባለፈ ልዩ መለያ ሊሆን አይገባም፡፡ ሲሆን ሲሆን ሁላችንም ከአንድ ቋንቋ በላይ መናገር መቻል ይገባናል፡፡ ለዚህም ተግተን መሥራት ይኖርብናል፡፡
የደቡቡ ሕዝባችን የክልል ግዛት የሚጠራበት ምንም ዓይነት የጎሳ መጠሪያ ስም የሌለው መሆኑ በራሱ ታላቅ ነገር ነው፡፡ የቀድሞ ግዛቶቻችን አርሲ፣ ወለጋ፣ ከፋ፣ ጎጃም፣ ባሌ፣ ኢሉአባቦር፣ ጋሞ ጎፋ፣ ወሎ፣ በጌምድር፣ ሸዋ፣ ትግራይ፣ ሐረርጌ፣ ወዘተ ስንል ምንም ዓይነት የጎሳ ስም እንደማያቀነቅን ሁሉ የግዛቱ ተወላጆችና ነዋሪዎች የሚጠሩት በግዛቱ ስም ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ሰው በውጭ አገር ኢትዮጵያዊ ተብሎ እንደሚጠራ ሁሉ እኔ ከወለጋ፣ ከባሌ፣ ከሸዋ፣ ከአርሲ፣ ከጎጃም፣ ከሶማሌ፣ ከአፋር፣ ከጋሞ ጎፋ፣ ከትግራይ፣ ከጋምቤላ፣ ከኢሉአባቦር፣ ከቤኒሻንጉል ጉምዝ፣ ወዘተ ፌዴራል ግዛት ነዋሪ ነኝ ማለት አይሻልምን?? ለምን ቢባል ሁላችንም ሰዎች ነንና፡፡ ከጥንት ዘመናት እስከ ግፈኛው ወታደራዊው ‹‹ደርግ›› እና አብዮታዊ ዴሞክራቱ ኢሕአዴግ ዘመነ መንግሥት ድረስ የኢትዮጵያ ሕዝቦች የጎሳና ቋንቋ ጉዳይ ሳይለያያቸው በአንድነት ‹‹እንደ ኢትዮጵያዊ ኖረዋል፣ ተዋግተዋል፣ ታግለዋል፣ ሲሞቱም ኢትዮጵያ›› ሆነዋልና፡፡  
በሌላ በኩል መንግሥታችን ደግሞ የግዛታዊ ፌዴራሊዝም አደረጃጀት፣ አወቃቀርና የሕግ ጉዳዮችን፣ ወዘተ የመሳሰሉትን በተመለከተ ግዛታዊ ፌዴራሊዝም ተግባራዊ ካደረገ እንደ አሜሪካ ወይም ጀርመን የሚቻለውን ሁሉ ለመማርና ለመቅሰም ማጥናት ይኖርበታል፡፡ በቴሌቪዥን መስኮት ብቅ በማለት የህንድን ፌዴራሊዝም ከእኛው ጋር በማስተያየት ተመሳሳይ ነው ብለው የሚናገሩ ተንታኞችን እናደምጣለን፡፡ እርግጥ ነው በህንድ ከ22 ያላነሱ ቋንቋዎች ይነገራሉ፡፡ እናም በህንድ የተተገበረው ፌዴራሊዝም ‹‹ፌዴራሊዝም መሰል›› (Quasi Federalism) ሲሆን፣ ያሉበትን ወደ አሥራ አምስት ገደማ የሚጠጉ ችግሮች ሲጠቅሱ ግን አይደመጥም፡፡ ትክክለኛው መንገድ ግን የተተገበሩትን የፌዴራሊዝም ዓይነቶች በጥንቃቄ በማጥናት ለእኛ ለራሳችን በሚበጀን መንገድ በማዋቀር መተግበር ይቻላል፡፡ የተከተልነው ፌዴራሊዝም ብዙ ያስተማረን ጉዳዮች ቢኖሩበትም፣ ተጠቃሚ ወገኖች የነበሩት ጥቂቶች ናቸው የሚል እምነት ተጠናክሮ ይሰማል፡፡  
ሕገ መንግሥት የማሻሻል ጉዳይ እንደ አዲስ ነገር አለመሆኑን በመቀበል የፌዴራል ሥርዓታችንን የማሻሻሉ ጉዳይ ከሕዝባችን የሰላም፣ የፍትሕ፣ የልማት፣ የኢኮኖሚና የማኅበራዊ አገልግሎት ተደራሽነትና የዴሞክራሲ መብት ተጠቃሚነት ጋር የተዛመደ በመሆኑ ችላ የማይባል ነው፡፡ ከዚህም በላይ ‹‹የራሳችንን ዕድል በራሳችን የመወሰን መብታችንን ተጠቅመን በነፃ ፍላጎታችን፣ በሕግ የበላይበትና በሕዝባችን ፈቃድ ላይ የተመሠረተ አንድ የፖለቲካ ማኀበረሰብ በጋራ ለመገንባት ቆርጠን ተነስተናል›› የሚለውን የሕገ መንግሥታችንን ዓላማ ለማሳካት ያስችለናል፡፡
ውድ አንባብያን የወቅቱ የአገራችን ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) አገራችንን ለመቀየር የሚያስችል ‹‹ሐሳብ›› ለሕዝብ አቅርበዋል፡፡ ይህንን ሐሳባቸውን የማይቀበሉ ብቻ ሳይሆን ለማደናቀፍ የሚሹ ወገኖች እንዳሉ ሁሉ፣ ‹‹ሐሳባቸውን›› የሚቀበሉ እጅግ በርካታ ወገኖች ስላሉ ይህንን የተቀደሰ ዓላማ ከዳር ለማድረስ ደጋፊያቸው ሕዝብ በቁርጠኝነት ከእኚህ መሪ ጎን መቆም የግድ ይለዋል፡፡ ምክንያቱም ባለፉት በርካታ ዓመታት የዘውዳዊው ሥርዓት፣ የወታደራዊው ‹‹ደርግ›› እና የኢሕአዴግ መንግሥታት ዘመናት እየተከማቹና እየተባባሱ የመጡትን የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የማኀበራዊ ችግሮችና ቀውሶችን በቀላሉ ለመፍታት የማይቻልበት ደረጃ ላይ ደርሰናልና፡፡
አገራችን ወደ ተረጋጋ ሰላም፣ የኢኮኖሚ ዕድገት፣ ብሎም ወደ ብልፅግና ለመሸጋገር እንድትችል የምንችለውን ሁሉ እኛው ራሳችን ማከናወን ይገባናል፡፡ ኩርፊያን አስወግደን፣ ይቅርታ ጠይቀን፣ ይቅር ተባብለን፣ የበደልናቸውን ክሰን ወደፊት መጓዝ ብቻ ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የወዳጅ አገሮች ድጋፍ ያስፈልገናል፡፡ በአገራችን የታመቀ የዕውቀት፣ የጉልበትና የተፈጥሮ ሀብት እንዳለን ይታወቃል፡፡ ነገር ግን የፌዴራል ሪፐብሊክ መንግሥታችን ላለፉት በርካታ ዓመታት ቢያንስ በአምስት መርሆች ዙሪያ ማለት ‹‹በእኩልነት፣ በፍትሕ፣ በመቻቻል፣ ሥራን በዕውቀት›› የመተግበሩ ጉዳይ ተስኖት ቆይቷል፡፡ ስለሆነም በርካታ የሕዝብ ጥያቄዎችን ለመመለስ የኢሕአዴግ መንግሥት አሁን እያገኘ ባለው የሕዝብ ድጋፍና ተሳትፎ በመጠቀም በቁርጠኛነት መሥራት የወቅቱ አጀንዳ እንዲሆን የግድ ይላል፡፡ ስለሆነም ሕዝባችን ከዚህ በታች የተዘረዘሩትን ጉዳዮች መንግሥታችን በሒደት ትኩረት እንዲሰጥባቸው ሲጠይቅ በርካታ ዓመታትን አሳልፏል፡፡
  • የሕግ የበላይነትና የፍትሕ መስፈን፣
  • የዴሞክራሲና ሰብዓዊ መብቶች መከበር፣
  • ሕዝባችን ከአገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገትና ማኀበራዊ አገልግሎት ያለአድልዎ ተጠቃሚነቱ መረጋገጥ፣
  • በሙስና የተዘፈቁ ባለሥልጣናት በሕግ የሚጠየቁበትን ሥርዓት መተግበር፣
  • በሕገወጥ መንገድ ሀብት ያካበቱ ሰዎች በሕግ የሚጠየቁበት ሁኔታ መፍጠር፣
  • የአገሪቱን ብሔራዊ ጥቅም፣ ዴሞክራሲና ሰብዓዊ መብቶችን በተመለከተ የፖለቲካ ፕሮግራም ቀርፀው በሕጋዊና በሰላማዊ መንገድ ለመወዳደርና በሕዝብ ምርጫ ሥልጣን ለመረከብ ለሚፈልጉ ኃይሎች የፖለቲካ ምኅዳሩን ማስፋት፣ ይህንን የማያሟሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚከስሙበትን ሁኔታ ማመቻቸት፣
  • የምርጫ ሥርዓቱ ፍትሐዊ የሚሆንበትን የሕግ አሠራር መተግበር፣
  • የኢትዮጵያን ሕዝቦች በጎሳና በቋንቋ የሚለያይ ሕጋዊ አሠራር የሚያከትምበት ሁኔታ መፍጠር፣
  • ወደፊት አንድ ጎሳ የአገሪቱን ሀብትና ሥልጣንን ጠቅልሎ የማይዝበት ሁኔታ ማረጋገጥ፣
  • ብሔራዊ መግባባት የሚፈጠርበትን መድረክ ማመቻቸት፣
  • የፖለቲካና የህሊና እስረኞች የሚፈቱበት ሁኔታ ማመቻቸት፣
  • እንደ ቀድሞ ዘመናት የሕዝባችንን አብሮና ተከባብሮ በፍቅርና በሰላምና የሚኖርበትን ባህልና ጉርብትና ማስጠበቅ፣
  • ኃላፊነትና ሥልጣን በዕውቀትና በችሎታ እንጂ በጎሳ ተዋፅኦ ወይም በግለሰብ ታማኝነት የማይሰጥበት የፖለቲካና ኢኮኖሚ ሥርዓት መተግበር፣
  • የወደፊትዋ ኢትዮጵያ ተረካቢ ወጣት ትውልድ ከአደንዛዥ ዕፅ፣ ከጫትና ከመጠጥ ሱስ የሚላቀቅበትን አገር አቀፍ እንቅስቃሴ መፍጠር፣
  • በተለያዩ የኤፍኤም ሬዲዮ ጣቢያዎች ወጣቱ በምዕራባውያን ባህል ተፅዕኖ ሥር እንዲወድቅ እየተሠራጩ ያሉትን ፕሮግራሞች ፈር በማስያዝ፣ ፕሮግራሞቹ ‹‹ትውልዱን የማዳን›› ሥራ እንዲሠሩ መደገፍ፣
  • የሕዝብ ጥያቄዎችንና ሐሳቦችን፣ የፖለቲካ ፓርቲ ፕሮግራሞችን፣ የተለያዩ ኅብረተሰባዊ ችግሮችን በተመለከተ ውይይቶችና ክርክሮችን ከመንግሥት ተፅዕኖ ውጪ እንዲካሄዱ ማበረታታት፣
  • ወገናዊነትን የማያራምዱ የሚዲያ ተቋማትንና የፕሮፌሽናል ጋዜጠኝነትን ማጠናከር፣
  • የመንግሥት ሲቪል ሰርቪስ አገልግሎት መንግሥታት በተቀያየሩ ቁጥር የሚቀያየር ሳይሆን፣ በሙያና በዕውቀት፣ በችሎታ፣ በመርህ ብቻ የሚመሩ እንዲሆኑ ማድረግ፣
  • የመንግሥት ሚኒስትር መሥሪያ ቤቶችንና የሕዝብ አገልግሎት ድርጅቶችን የሚመሩ ኃላፊዎች በግልጽ ከሚታወቁ የትምህርት ተቅዋሞች የተመረቁና እውነተኛ ማስረጃ ያላቸው ሆነው በሙያቸው በችሎታቸና በብቃታቸው በዕውቀታቸው እንዲመደቡ ማድረግ፣
  • ወጣቱ ትውልድ ስለአገሩ ባህልና ታሪክ፣ ትውፊት፣ ስለቀድሞ መሪዎቻችን፣ አርበኞቻችን፣ ጀግኖቻችን፣ ምሁሮቻችን፣ ሊቃውንቶቻችን፣ የኪነ ጥበብ ሰዎቻችን፣ ወዘተ ገድልና ተጋድሎ የሚያውቅበትና የሚማርበትን መድረክ ማመቻቸት፡፡
  • ለአገራችን ዕድገት መሠረት የግብርናው ዘርፍና የማምረቻ ኢንዱስትሪዎች መጠናከር ሲሆን፣ ኢትዮጵያውን ባለሀብቶች በእነዚህ ዘርፎች ያለ መድልዎ በሰፊው የሚሳተፉበትን ሁኔታ ማመቻቸት፣
  • ማንኛውም የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሐሳብና የዕውቀት መፍለቂያዎች በመሆናቸው የአካዳሚክ ነፃነታቸውን ያለምንም ገደብ ማስከበርና ማስጠበቅ፣ ወታደሮች በዩኒቨርሲቲ ግቢዎች የማይሰፍሩበትን ሕግ መተግበር፣
  • መንግሥትና ሃይማኖት በሕገ መንግሥታችን ተለያይተዋል ቢባልም ከመጋረጃ ጀርባ በመሆን የሃይማኖት ተቋማት አመራርን የመቆጣጠር ድርጊት መቆም አለበት፣
  • የሃይማኖት አክራሪነት ሊያመጡ የሚችሉትን ችግሮች መንግሥት ሕዝብን በማወያየትና በማሳተፍ ለሰላምና ለመቻቻል ለመከባበር መሥራት ይኖርበታል፡፡
የሃይማኖት ተቋማት ከመልካም እምነት አስተምሯቸው ባሻገር ሃይማኖቱን የገንዘብ መሰብሰቢያ ዘዴ በማድረግ የሚካሄደውን የሕዝብ ዘረፋ የመከላከል ኃላፊነት መውሰድ አለበት፡፡  
ውድ አንባብያን
ይህ ጽሑፍ የአገራችንን የፌዴራሊዝም ችግሮች በተመለከተ በሦስት ክፍሎች ለቀረበው ሐሳብ ማጠቃለያው ሲሆን፣ ያቀረብኳቸው ሐሳቦች ላለፉት 27 ዓመታት በሕዝባችን ውስጥ ሲብላሉ የቆዩ ናቸው፡፡ በተነሱት ጉዳዮች የማይደሰቱ ይኖራሉ፡፡ ያቀረብኳቸውን ሐሳቦች የማይደግፉ ወገኖች እንደሚኖሩ ሁሉ የሚደግፉም ይኖራሉ፡፡ በአንዳንድ የአገላለጽ ዘይቤዎቼ ቅር የተሰኙ ወይም የተከፉ ካሉ ይቅርታ እየጠየቅሁ፣ ባሳለፍናቸው ዘመናት በርካታ ሐሳቦች ሲቀርቡ ይህ ‹‹የትምክህተኞች›› ወይም ‹‹የጠባቦች‹‹ ነው እያልን በመሳደብና በማንኳስስ መልካም ሐሳቦችና ብዙ ምክሮች በከንቱ ቀርተዋል፡፡
ከሚያዝያ 24 ቀን 2010 ዓ.ም. ጀምሮ በአገራችን የፖለቲካ መድረክ ኢሕሕዴግ አዲስ ምዕራፍ ከፍቷል ሊባል ይቻላል፡፡ አንዳንድ ሊነገሩ ቀርቶ ሊታሰቡ የማይቻሉ ጉዳዮችን ከኢሕአዴግ እየሰማን ነው፡፡ መስማት ብቻ ሳይሆን የተግባር ጅማሮም ጭምር እያየን ነው፡፡ ስለሆነም እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ሆኖ ለኢትዮጵያ ሕዝብ የመጣውን ይህን የለውጥ ሒደት ማቆም ስለማይቻል፣ በቀናነትና በአዎንታ ተቀብለን በሚቻለን ሁሉ የለውጥ ሒደቱን በመደገፍ መሳተፍ ይኖርብናል፡፡ ፈጣሪ እግዚአብሔር ሕዝብህን አድን፣ ኢትዮጵያን ባርክ፣ ከፍ ከፍም አድርገን!

No comments:

Post a Comment