Pages

Tuesday, May 22, 2018

ኢትዮጵያ እና አሳሳቢው የፊልም እንቅስቃሴዋ

በጥበቡ በለጠ

የሰው ዘር መገኛ ናት የምትባለው ኢትዮጵያ ይህን የሚያክለውን ታሪኳን ገና በደንብ አላስተዋወቀችውም፡፡ ጽላተ ሙሴ ከኔ ዘንድ ነው የምትለው ኢትዮጵያ እስካሁን ወደ አለማቀፍ ስምና ዝና አልመጣችም፡፡ ገና በሰባተኛው መቶ ክፍለ-ዘመን የእስልምና ሀይማኖት በአለም ላይ ሰፊ አድማሱን በሚያሳይበት ወቅት ኢትዮጵያ የነብዩ መሐመድ ቤተሰቦች መቀመጫ የሆነችው ኢትዮጵያ ታላቅ ፊልም አልሰራችበትም፡፡ የቅዱሳንና የታላላቅ መሪዎች ምድር የሆነችው ኢትዮጵያ ተአምራዊት ሀገር መሆንዋን በአደባባይ አላሳየችም፡፡ የጥቁር ህዝብ ሁሉ የነጻነት ተምሳሌት የሆነችው ኢትዮጵያ ታሪኳን ለጥቁሮች በሚገባ ገና አላስተማረችም፡፡ ገና ብዙ ብዙ ማስታወቂያዎች ይቀሯታል፡፡ የራስዋን ታሪክ እያጠፋች በቱርክ የፊልም ታሪኮች ተወራለች፡፡


ኢትዮጵያ ውስጥ ዛሬ በህይወት የሌለ አንድ ተቋም ነበር። ይህም የኢትዮጵያ ፊልም ኮርፖሬሽን እየተባለ ይጠራ የነበረ ነው። የኢትዮጵያ ፊልም ኮርፖሬሽን ከታህሣስ 11 ቀን 1979 ዓ.ም ጀምሮ መቋቋሙን የጊዜያዊ ወታደራዊ አስተደደር ደርግ ስለ ፊልም ስራዎች በነጋሪት ጋዜጣ በቁጥር 306/1979 ያወጣው አዋጅ ይገልፃል። በአዋጁ መሠረት፤ “የኮርፖሬሽኑ ዓላማ በሀገሪቱ ውስጥ የፊልም ስራን ማደራጀት፣ ማስፋፋትና ማካሄድ ሲሆን፤ ዋና ዋና ተግባራቱም፤

- ፊልም ማስመጣት፣
- ፊልም ማከፋፈል፣
- ፊልም ማሳየት፣
- ፊልም ማምረት፣
- የፊልም ቤቶችንና የፊልም ማሣያ ቦታዎች ማቋቋምና ማስተዳደር፣
- የፊልም ዝግጅትና ኢንደስትሪ የሚዳብርበትን የማጥናትና ጥናቱና አስፈላጊው በጀት ሲፈቀድ ተግባራዊ ማድረግ ናቸው። 



ሌሎችም በርካታ ዓላማዎች ነበሩት ኰርፖሬሽኑ። ነገር ግን በዘመነ ኢህአዴግ ድርጅቱ አትራፊ አይደለም ተብሎ በፓርላማ ውሳኔ እንዲፈርስ ተደረገ። ይህ የኢትዮጵያ ፊልም ኮርፖሬሽን በህይወት በነበረበት ወቅት አያሌ ተግባራትን አከናውኗል። የተለያዩ ዶክመንተሪና ተራኪ ፊልሞችን ሠርቷል። ባለሙያዎችን አፍርቷል። ጥናትና ምርምር አድርጓል።

የዚህ የፊልም ኮርፖሬሽን የጥናት ጽሁፎች አንዳንዶቹ እጄ ላይ አሉ። እናም ባነበብኳቸው ቁጥር ድርጅቱ በጥሩ እንቅስቃሴ ውስጥ እንደነበር እገነዘባለሁ። እናም አሁንም ቢሆን በመንግስት በኩል የሀገሪቱን ቅርሶች እና መልካም ገፅታዎች በተደራጀ መልኩ ፊልም እየሠሩ ለማስቀመጥ እንዲህ ዓይነት ተቋሞችን መፍጠርና ማጠናከር ይገባዋል እላለሁ።

እርግጥ ነው በርካታ የፊልም ድርጅቶች በኢትዮጵያ ውስጥ ተመስርተዋል። ሁሉም ማለት ይቻላል የግል ናቸው። በግል የሚመሠረቱ ተቋሞች ደግሞ ዋነኛ ትኩረታቸው ገቢ ማስገኘት እና ህልውናቸውንም ማስጠበቅ ነው። ስለዚህ እንቅስቃሴያቸው ሁሉ ከገንዘብ ጋር የተያያዘ ነው። በዚህም የተነሳ የኢትዮጵያ ታላላቅ ቅርሶች እና ታሪኮች በስርዓት የሚዘክራቸው አካል ጠፍቷል ማለት ይቻላል።

በልዩ ልዩ የአውሮፓና የአሜሪካ ሀገራት እንዲሁም በሩቅ ምስራቅም ያሉትን ህዝቦች ስናይ እንዲህ ዓይነት ታሪኮችን የሚሰሩባቸው የጥናትና የምርምር ተቋማት አሏቸው። እነዚህ የጥናትና ምርምር ተቋሞች ደግሞ የከፍተኛ ትምህርት መስጫ ስፍራዎች ማለትም ዩኒቨርሲቲዎች ናቸው። ዩኒቨርሲቲዎቻቸው ባሏቸው የፊልም ዲፓርትመንቶች አማካይነት ፊልም ይቀርፃሉ። ታሪክ፣ ባህል፣ ቅርስ፣ ማንነትን ወዘተ ሰርተው በአርካይቭ ውስጥ በማኖር ለቀጣይ ትውልድ ያስቀምጣሉ። ከዚሁ ጋርም በሌሎች ሀገሮች ውስጥ የተሰሩ ታሪካዊ፣ ባህላዊና ጥንታዊ ፊልሞችን በመሰብሰብ ሁሉ ያስቀምጣሉ።

ለምሳሌ ያህል በአሜሪካን ሀገር የታተመው “American Film Institute Catalogue” የተሰኘ መጽሐፍ አለ። በዚህ መጽሐፍ ውስጥ በዓለማችን ላይ ታላላቅ የሚባሉት ዶክመንተሪ ፊልሞች ተመዝግበዋል። ከእነዚህም ውስጥ ደግሞ አሜሪካ ውስጥ የሚገኙት የትኞቹ እንደሆኑ እና የት የት ቦታ እንደሚገኙ ይጠቁማል። ስለ ፊልሞቹም አጫጭር መግለጫ ይሰጣል። በጣም የሚገርመው ደግሞ በኢትዮጵያ ላይ ትኩረት አድርገው የተሰሩ ጥንታዊ ዶክመንተሪዎች ሁሉ በዚህ መጽሐፍ ውሰጥ ተመዝግበዋል።

በእንግሊዝና በፈረንሣይም እንዲሁ ዓይነት ተመሣሣይ ታሪክ እናገኛለን። የራሳቸውን ታሪክና አስተሳሰብ ከመሰብሰብና ከመስራት አልፈው የሰው ሀገርን ትልልቅ ቅርሶች ማስቀመጥ ከጀመሩ ዘመናት ተቆጥረዋል። ለምሳሌ እ.ኤ.አ በ1909 ዓ.ም ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ አጤ ምኒልክን በፊልም የቀረፃቸው ፈረንሣዊ ቻርልስ ማርቴል ይባላል። ይህ የአጤ ምኒልክ ፊልም በዓለማችን ላይ በቀደምትነት ከተቀረፁት ፊልሞች መካከል አንዱ ነው። በዚህ ፊልም ውስጥ አጤ ምኒልክን ማየት እንችላለን። ግን ይህ ፊልም የሚገኘው ከፓሪስ ከተማ ወጣ ብሎ በሚገኘው እጅግ የተከበሩና የተወደዱ ቅርሶች በሚቀመጡበት “Archives Des Films” ተብሎ በሚታወቀው ማዕከል “Bois D’Arcy” ውስጥ ነው።

እ.ኤ.አ በ1917 ዓ.ም የንግስተ ነገስታት ዘውዲቱ ምኒልክ ንግስና በሚከበርበት እለት በፊልም ተቀርጿል። ዛሬ ንግስት ዘውዲቱን በፊልም ልናያቸው እንችላለን። ነገር ግን ይህ ፊልም በእጃችን ላይ የለም። የሚገኘው በእንግሊዝ ሀገር ብሔራዊ የፊልም ማህደር /National Film Archives/ ውስጥ ነው። እንዲህ በቀላሉ ማንም ሊያየው አይችልም። በርካታ መስፈርቶችን ማሟላት ግድ ይላል።

በጀርመን ሀገር ደግሞ ኢትዮጵያን የተመለከቱ እጅግ በርካታ ጥንታዊ ፊልሞችን እናገኛለን። እ.ኤ.አ በ1927 ዓ.ም የተሠራው ጥንታዊ ፊልም አንዱ ነው። ይህ ፊልም በደቡብ ኢትዮጵያ ውሰጥ ከሚገኙት ማኅበረሰቦች አንዱ በሆነው በዲሜ ብሔረሰብ ላይ መሠረት ተደርጐ የተሰራ ነው። ዲሜዎች ከጥንት እስከ ዛሬ የሚታወቁበት ደግሞ የብረት ማዕድንን ከመሬት ውስጥ በማውጣት አቅልጠውና ቀጥቅጠው ቅርፅ በማውጣት ልዩ ልዩ መሣሪያዎችን መስራት ነው። እናም በ1918 ዓ.ም አካባቢ ጀርመኖች ዲሜ ድረስ ሄደው ፊልም ቀርፀዋል።

የኢትዮጵያ እና የጣሊያን ጦርነት ገና ከዝግጅቱ ጀምሮ ጀርመኖች ቀርፀው አስቀምጠውታል። ከ300 በላይ የኢትዮጵያ ዶክመንተሪ ፊልሞች በአውሮፓ ውስጥ ይገኛሉ። ሁሉንም መዘርዘር ስለማይመች እንጂ መረጃዎቹን ሰብስቤያቸዋለሁ። ለምሳሌ በ1916 ዓ.ም Edward Salisbury የተባለ ፊልም ሰሪ ኢትዮጵያ ውሰጥ መጥቶ “The Lost Empire” የተሰኘ ዶክመንተሪ መስራቱ ተፅፏል። እንዳውም ይህ ፊልም በ1921 ዓ.ም በጃንዋሪ ወር ኒውዮርክ ውስጥ መታየቱን ዘገባዎች ያመለክታሉ። ይህ ፊልም New York’s Natural History Museum ተብሎ በሚጠራው ማዕከል ውስጥ ይገኛል።

ይህን ሁሉ ዝርዝር ያመጣሁት እስካሁን ድረስ በሀገራችን ኢትዮጵያ ፊልምን በተመለከተ በመንግስት ተቋማት በኩል ትኩረት የተሰጠው አጀንዳ ስላልመሰለኝ ነው። ለምሳሌ አዲስ አበባ ውስጥ ያለውን ብሔራዊ ሙዚየም እና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ውሰጥ የሚገኘውን የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም ሙዚየሞችን እንቃኝ። በእነዚህ ሙዚየሞች ውስጥ አያሌ ቅርሶች ቢኖሩም ፊልምን በተመለከተ ግን እዚህ ግባ የሚባል መረጃ ማግኘት አይቻልም።

በኢትዮጵያ ውስጥ ዶክመንተሪ ፊልሞችን በመስራት የሚታወቁ አለማቀፍ ፕሮዳክሽኖች የሉንም፡፡ በሀገሪቱውስጥ ያሉት ፕሮዳክሽኖች አስፈላጊው ድጋፍና ትኩረት ስለማይሰጣቸው እድገታቸው ጠንካራ ሆኖ አይታይም፡፡ በሀገር ውስጥ ያሉት ፕሮዳክሽኖች የሚሰሯቸው ፊልሞች በኢትዮጵያ ታሪክና ባህል ላይ ያተኰሩ ቢሆኑም ራሳቸውን ለማቆም ገቢ ያስፈልጋቸዋልና ለትርፍ የሚሰሩ ናቸው። ስለዚህ ከገቢ አንፃር በሚያዋጧቸው የሥራ መስኰች ላይ ብቻ ነው አፅንኦት የሚሰጡት። እርግጥ ነው እነዚህ ፕሮዳክሽኖች እስካሁን የሰሯቸው የኢትዮጵያ ዶክመንተሪ ፊልሞች የሀገሪቱን ቅርስ በማስተዋወቅና በመመዝገብ እንዲሁም ፈልፍሎ በማውጣት ያበረከቱት አስተዋፅኦ ከፍተኛ ነው። ነገር ግን የመንግስት ተቋማት የሆኑት ባህል ሚኒስቴርና ዩኒቨርሲቲዎች እንዲሁም ሌሎችም የሚመለከታቸው አካላት የኢትዮጵያን ታሪካዊ እውነቶች በፊልም ሰርቶ የማስቀመጥ እንቅስቃሴያቸው እስከ አሁን ድረስ ፈፅሞ ደካማ ነው ብሎ መናገር ይቻላል።

አንድ የማይካድ ነገር ደግሞ አለ። ለምሳሌ በባህል ሚኒስቴር ስር የሚገኘው የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን መስሪያ ቤት በተለያዩ የጆርናል እና የጥናት ህትመቶች የኢትዮጵያን ታሪክና ማንነት ሲያሳይ ቆይቷል። ይሁን እንጂ እነዚህ ጥናቶች በፊልም ተደግፈው ገና አልተሰሩም። በዚሁ መ/ቤት የታተመው “ዜና ቅርስ” የተሰኘው መጽሔት የካቲት 2002 ዓ.ም ባወጣው ዘገባ “በሰው ዘር አመጣጥ አዲስ ግኝት ተመዘገበ” የሚል ዜና ይዞ ወጥቷል። ዜናው አንዲህ ይላል፤

ከኢትዮጵያና ጃፓን የተውጣጡ ሳይንቲስቶች በአፋር ሸለቆ ደቡባዊ የመጨረሻ ክፍል አካባቢ በኦሮሚያ ክልል ጭሮ ዞን በተደረገው የመስክ ጥናት 10 ሚሊዮን ዓመት ዕድሜ ያለውና የሰው ዘር መነሻ የሆኑ የጥንት ዝርያዎች ሁሉ መጀመሪያ የሆነ ግኝት እንደሆነ ጽሁፉ ይገልፃል። ይህ የቅርስ መጽሔት ዜና ሲያክልም፤ ግኝቱ ከቺፓንዚ ጐሬላ /APE/ የዘር መስመር የተለየና በወቅቱ የኖሩ ቅሪቶች በጣም የተወሰኑ እና እስካሁንም ድረስ ጥቂት የመንጋጋ ስብርባሪ ጥርሶች በኬንያ ብቻ እንደተገኘ ይገልፃል።

ቀደም ሲል የተገኙት 6 ሚሊዮን ዓመታት ዕድሜ ያላቸው ቅሪተ አካል ሲሆኑ አዲሱ ግኝት የኢትዮጵያን የሰው ዘር አመጣጥ ጥናት ሪኰርድ ወደኋላ በመሄድ ማዮሲን /Miocene/ በተባለ የጂኦሎጂ ዘመን ውስጥ አስገብቶታል በማለት ጽሁፉ ያብራራል። ታዲያ እንዲህ ዓይነት እጅግ አስደናቂ ግኝት ሲካሄድ እንዴት ዶክመንተሪ ፊልም አይሰራበትም? እንዴትስ ዓለም እንዲያውቀው ታላላቅ ሚዲያዎችን ጋብዞ እንዲሰሩበት አይደረግም እያልኩ አስባለሁ።

በተለይ በአርኪዮሎጂ እና በአንትሮፖሎጂ የጥናት መስኮች ኢትዮጵያን በሰፊው የሚያስተዋውቁ ግኝቶች አሉ። እነዚህን ግኝቶች በዶክመንተሪ ፊልም ካልሰራናቸው እና ልዩ ልዩ ሀገራት ውስጥ በሚካሄዱ የፊልም ፌስቲቫሎች ላይ እንዲታዩ ካላደረግን በፊልም ኢንደስትሪው መስክ የምናደርገው ጉዞ አሁንም የእንፉቅቅ ነው የሚሆነው። ሩቅ አሳቢ፣ ሩቅ አላሚ የሆነ የጥበብ መሐንዲስ ያስፈልገናል።

No comments:

Post a Comment