Pages

Wednesday, May 23, 2018

የኢትዮጵያ እግር ኳስና የምርጫ ጨረታ

የኢትዮጵያ እግር ኳስና የምርጫ ጨረታ
ሲንከባለል የቆየው የእግር ኳሱ ብሔራዊ ፌዴሬሽን የአመራሮች ምርጫ ለመጨረሻ ጊዜ ለግንቦት 25 ተቀጥሯል
በካምቦሎጆ ዙሪያ ከወትሮው ለየት ባለ መልኩ የደራና የጦፈ የድለላ ሽሚያ የሚስተዋልበትን ክስተት ከመጋረጃ ጀርባ እያስተናገደ ይገኛል፡፡ የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንታዊና የሥራ አስፈጻሚ ኮሜቴ ምርጫ ባልተከናወነበት በዚህ ወቅት፣ ጉዳዩ ለጨረታ የቀረበ እስኪመስል የተቋሙ የዋና ጸሐፊነት ቦታና ሌሎችም በንዑስ ኮሚቴ የሚመሩ ልዩ ልዩ ክፍሎች በእነማን እንደሚመሩ ከወዲሁ ለእነማን እንደሚሆን መቃወቅ የጀመረ ይመስላል፡፡

ለእግር ኳሱ ብዙም ግድ የማይሰጣቸው አንዳንድ አማተር ሹመኞች፣ በካምቦሎጆ ዙሪያ የሚያደርጉት ቅስቀሳና ቁስቆሳ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ በፌዴሬሽኑ ልዩ ልዩ ንዑሳን ክፍሎች የአመራርነት ሚናን ለማቆጣጠር እየተከናወነ የሚገኘው በኔትወርክ የተሳሰረ ዘመቻ  ለእግር ኳሱ ቀጣይ ሕልውና ከወዲሁ የሥጋት ምንጭ እየሆነም ይገኛል፡፡
አሁንም ካለውና ለወራት ለዘለቀው የእግር ኳሱ ውዝግብና ጡዘት ዓይነተኛ ሚና በመጫወት የአንበሳውን ድርሻ የሚወስደው የስፖርቱ መዋቅራዊ ይዘትና አመራሩ ለመሆናቸው በተለያዩ ጊዜያት የቀረበው ዳሰሳ ጥናት ማረጋገጫ መሆኑ አያከራክርም፡፡ ለችግሩ መንስዔ ተብለው ውግዘትና ወቀሳ እየቀረበባቸው የሚገኙ በተለይም አገልግሎቱን ያጠናቀቀው የፌዴሬሽኑ አመራር መካከል አብላጫውን ቁጥር የሚይዙት፣ ተቋሙን ለሁለተኛ ጊዜ ለማገልገል የሚያስከትል የክልል ውክልና ተሰጥቷቸው ለምርጫ ቀርበዋል፡፡
ለዚህ ደግሞ ትልቁን ድርሻ እየተጫወቱ የሚገኙት የዕለት ዕለት እንቅስቃሴያቸውንና ውሎዋቸውን በአዲስ አበባ ካምቦሎጆ ዙሪያ ያደረጉ አጫራቾች ለመሆናቸው የአደባባይ ምስጢር ከሆነ ውሎ አድሯል፡፡
በእግር ኳስ ዳኝነት አህጉራዊና ዓለም አቀፍ ውድድሮችን መምራት የሚያስችል የሙያ ፈቃድ ካላቸው ሙያተኞች ይጠቀሳሉ፡፡ የምርጫው የኃይል አሰላለፍ ባልታወቀበት በዚህ ወቅት ማንነታቸውን ለመግለጽ ግን ፈቃደኛ አይደሉም፡፡ ይሁንና በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በተለይም ክቅርብ ዓመታት ወዲህ እየተስተዋለ ለሚገኘው ለስፖርቱ አስተዳደር ውድቀት፣ ግልፅነትና ተጠያቂነት አለመኖር መሆኑን ያምናሉ፡፡ የከረመው አጨቃጫቂ የሥራ አመራር ምርጫ ላይ በአናቱ በቀጣይ ለሚጠበቀው የጽሕፈት ቤት ተጠሪዎች፣ በጽሕፈት ቤት አካባቢ የሚመደቡ ባለሙያዎችና ሌሎችም በስፖርቱ አመራር ዙሪያ ለመሰባሰብ ያሰፈሰፉ ግለሰቦች ቃብድ ለማስያዝ በካምቦሎጆና አካባቢው መብዛታቸውን ሙያተኛው ይጠቅሳሉ፡፡
ከሳምንት በፊት በአዲስ መልክ የተሰየመው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስመራጭ ኮሚቴ፣ ኃላፊነቱን በይፋ ከጀመረበት አንስቶ የዕቅድ ክንውኑን ካልሆነ ክልሎች እነማንን ዕጩ  ተወዳዳሪ አድርገው እንደላኩ የሚለውን ኮሚቴው ምንም ዓይነት መግለጫ እንዳልሰጠ ይታወሳል፡፡ በካምቦሎጆ ዙሪያ የሚገኙ አጫራቾች ግን የአስመራጭ ኮሚቴው የዕለት ተዕለት ውሎና እንቅስቃሴ ለእነሱ የአደባባይ ምስጢር መሆኑን የሚናገሩት ሙያተኛው፣ ‹‹አይደለም የፌዴሬሽኑ ተወዳዳሪዎች ማንነትና ቀጣዩ አመራር እነማን የካቢኔው አባል እንደሚያደርጉ ያውቃሉ፤›› ይላሉ፡፡
እነዚህ አካላት በየስታዲየሙ የተንሰራፋውን ብልሹ አሠራርና አካሄድ ለዘለቄታው ከማረም ይልቅ፣ በካምቦሎጆ ዙሪያ በኮፍያ ተከልለው እነማን ወደ ስፖርቱ መምጣት እንዳለባቸው፣ እነማን ከመድረኩ መገለል እንደሚጠበቅባቸው የሚሾሙና የሚሽሩ ለመሆናቸው በየባንኮኒው ጭምር ሥራ በዝቶባቸው ይታያሉ፡፡
የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንታዊና የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ምርጫ፣ ግንቦት 26 ቀን 2010 ዓ.ም. በአፋር ሰመራ ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ከሳምንት በፊት በካፒታል ሆቴል የተሰየመው አስመራጭ ኮሚቴ፣ ክልሎች የሚያቀርቡዋቸውን ተወዳዳሪዎች ዝርዝር ማክሰኞ ግንቦት 14 ቀን 2010 ዓ.ም. ይፋ እንደሚያደርግ አስታውቋል፡፡ ከዕጩ አቀራረብ ጋር ተያይዞ ቅሬታዎች የሚመጡ ከሆነ ደግሞ ግንቦት 15 ቀን ቀርቦ፣ ግንቦት 18 ቀን ጉዳዩን የአስመራጭ ኮሚቴው ይግባኝ ሰሚ ማብራሪያ እንደሚሰጥ ጭምር አብራርተዋል፡፡ የመጨረሻዎቹ ዕጩ ተወዳዳሪዎች ዝርዝር ደግሞ ግንቦት 20 ቀን ይፋ እንደሚሆንም አስታውቋል፡፡
ይሁንና ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ድረስ፣ ለፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ከሚጠበቁት ክልሎች በስተቀር፣ ቀሪዎቹ ክልሎች ተወዳዳሪዎቸቸውን ማሳወቃቸው እየተነገረ ይገኛል፡፡ ምንም እንኳ ቀደም ሲል የቀረቡት ዕጩ ተወዳዳሪዎች እንደነበሩ፣ የአዲስ አበባና የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮች ሁለት፣ ሁለት ተጨማሪ ዕጩ ተወዳዳሪዎችን አቅርበዋል፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ ኢንጂነር ፀደቀ ይሁኔን ለፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ሲያቀርብ፣ የቀድሞ የአዲስ አበባ ወጣቶችና ስፖርት ኮሚሽነር አቶ ተስፋዬ ኦሜጋ ለሥራ አስፈጻሚ ምርጫ ማቅረቡ ታውቋል፡፡ የድሬዳዋ ከተማ በበኩሉ ዶ/ር ወገኔ ዋልተንጉሥና አቶ ወንዳወክ አበዜን ከአቶ አበበ ገላጋይ በተጨማሪ ለሥራ አስፈጻሚነት ምርጫው ማቅረቡ ታውቋል፡፡ የትግራይና የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች ቀደም ሲል ያቀረቧቸውን ዕጩ ተወዳዳሪዎች በነበሩበት እንደሚቀጥሉ ቀሪዎቹ ክልሎች ግን የዕጩ ማቅረቢያው ቀን እስከ ቅዳሜ ግንቦት 11 ቀን 2010 ዓ.ም. ድረስ የዕጩዎቻቸውን ማንነት ለመግለጽ ፍላጎት አላሳዩም፡፡
ምክንያቱ ደግሞ ክልሎቹ በሚያቀርቧቸው ዕጩዎች ማንነት ላይ መግባባት ካለመቻላቸው በተጨማሪ ሌሎች ክልሎች እነማን አቀረቡ የሚለው በምስጢር ለመያዝ እንደሆነም ሲነገር ሰንብቷል፡፡
በዓለም አቀፉ እግር ኳስ ማኅበር (ፊፋ) ትዕዛዝ እንዲበተን በተደረገው በቀድሞ አስመራጭ ኮሚቴ አማካይነት ተገቢው ማጣራት ተደርጎባቸው ለምርጫው እንደሚቀርቡ ይፋ ተደርገው የነበሩት ዕጩ ተወዳዳሪዎች፣ ለፕሬዚዳንታዊ ምርጫው አቶ ጁነዲን ባሻ ከድሬዳዋ፣ አቶ ተካ አስፋው ከአማራ፣ ዶ/ር አሸብር ወልደጊዮርጊስ  ከደቡብ፣ አቶ ዳግም መላሸን ከጋምቤላ፣ አቶ ኢሳያስ አደራ ከኦሮሚያ፤ ለሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ደግሞ፣ አቶ ዮሴፍ ተስፋዬ፣ አቶ አሥራት ኃይሌና ሲስተር ኃይለየሱስ ፍስኃ ከአዲስ አበባ፣ አቶ ሰውነት ቢሻውና ዶ/ር ሲራክ ሀብተማርያም  ከአማራ፣ አቶ አበበ ገላጋይ ከድሬዳዋ፣ አቶ ከማል ሁሴንና ዶ/ር ኃይሌ ኢቴቻ ከኦሮሚያ፣ አቶ አላሚራህ መሐመድ ከአፋር፣ አቶ ዘሪሁን ቀቀቦ ከደቡብ፣ አቶ ወልደገብርኤል መዝገቦና ኮሎኔል አወል አብዱራሂም ከትግራይ፣ ወ/ሮ ሶፊያ አልማሙ ከቤኒሻንጉል፣ ዶ/ር ቻን ጋትኮት ከጋምቤላ፣ አቶ ኢብራሂም መሐመድ ከሐረሪና አቶ አብዱራዛቅ ሐሰን ከኢትዮ ሶማሌ መሆናቸው ይታወቃል፡፡

No comments:

Post a Comment