Pages

Monday, May 28, 2018

የአማራ ብሔረተኛነት ከየት ወዴት?

 

ደረጀ ይመር  
ዛሬ ዛሬ ዜጎች በሐሳብ ወይም በምክንያት ከመቀራረብ ይልቅ ለስሜት ወይም ለምንዝላታዊ መሳሳብ (primordial connection) ቅርብ ለሆነው ዘውጌ ማንነታቸው (ethnic identity) ፊት መስጠትን ይመርጣሉ፡፡ እንደ ድርና ማግ ባስተሳሰረን ኢትዮጵያዊ ማንነት ኪሳራ፣ በጥቃቅን አካባቢያዊ ሽኩቻዎች ላይ ተጠምደናል፡፡ የዘውጌ - ማንነት ጉዳይ ሁሉም  በየአቅጣጫው የሚጮኽበት አጀንዳ መሆን ከጀመረ ከራርሟል፡፡

እንደሚታወቀው በጠባብ ማንነት ዙሪያ የተደራጁ የፖለቲካ ቡድኖች በአንድ ሀገር ውስጥ በተበራከቱ ቁጥር በእዛው ልክ የእልቂት ነጋሪትን የሚጎስሙ ጽንፈኛ የዘውግ ፖለቲካ አምላኪዎች በሚያስበረግግ ደረጃ እየፋፉ ይሄዳሉ፡፡
በዚህም የተነሳ በሀገራዊ አርበኝነት መቃብር ላይ ዘውጌ ብሔረተኛነት ይጎመራል፡፡ የጠነከረ ጎጠኝነት፣ ከጠነከረ ሀገራዊ አርበኝነት ጋር በፍጹም ታርቆ ስለማይሄድ፣ የግድ በአንዱ ሞት ሌላው እስትንፋሱን ይቀጥላል፡፡ ዘውጌ ብሔረተኛነት (ethnic nationalism) በባሕሪው በከበባ ስነልበና (siege mentality) የተቀየደ ስለሆነ ከሌሎች መሰል ሕዝቦች ጋር የሚያዛምደውን የአንድነት ድልድይ እያፈራረሰ፣ የራሱን ደሴት ለመቀለስ የሚታትር አውዳሚ የፖለቲካ አቅጣጫ ነው፡፡
ለሀገራዊ አርበኝነት መደላደል ጠንካራ መሠረት በሆነው በአማራው ሕዝብ ዙሪያ  የተሰባሰቡ ቡድኖች ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እያቀነቀኑት ያለው የዘውጌ ፖለቲካ ገሀድ እየሆነ እየመጣ ነው፡፡ የአማራ ሕዝብ በቋንቋ፣በባህል፣በሃይማኖትና በጋብቻ ከሌሎች የሀገራችን ሕዝቦች ጋር በፈጠረው መስተጋብር የተነሳ  ለዘውጌ ማንነት ባዕድ ሆኖ የኖረው፡፡ አጥንትና ዘር ቆጥሮ ወደ ውስጥ ከሚቀነበብ ዝግ ሥነ ልቦና ይልቅ ወደ ውጪ የሚመለከት አቃፊ ማንነትን ተላብሷል። የአማራው ዘውግ እንደ ጥላ አሰባስቦ የያዘውን ኢትዮጵያዊ ማንነቱን በየትኛውም የታሪክ አጋጣሚ ለድርድር አቅርቦ አያውቅም፡፡ የእናት ሀገሩን ነፃነት ለማስጠበቅ በየጋራ፣በየተረተሩ ደምና አጥንቱን ያለ ስስት ገብሯል፡፡ ጎንደሬውን፣ወለየውን፣ሸዋውንና ጎጃሜውን ያስተሳሰረው ገመድ ኢትዮጵያዊ ቀለም እንጂ አማራነቱ አልነበረም፡፡ በኢትዮጵያ የታሪክ ሒደት ውስጥ ራሱን በአማራ ስነ ልቦና ያሰባሰበ ሕዝብ ኖሮ እንደማያውቅ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማሪያምን ጨምሮ ብዙ ልሂቃን ይስማማሉ፡፡ የአማራ ብሔረተኞች ግን ይህንን እውነታ እንደ ክህደት ነው የሚቆጥሩት፡፡ ለመሆኑ ለአማራ ብሔረተኛነት መነቃቃት እንደ ምክንያት የሚወሰዱት ምንድን ናቸው?

ፀረ- አማራ ተረክ
ፋሺስት ኢጣሊያ ኢትዮጵያን ዳግም በወረረበት ወቅት የሀገራችንን ሕዝቦች ልቦና ለመስለብ እንደ ፕሮፓጋንዳ ሲጠቀምባቸው ከነበሩት ዘዴዎች መካከል በዋነኛነት የሚጠቀሰው የፀረ-አማራ ተረክ ነበር፡፡ “የጣሊያን መንግሥት ኢትዮጵያን በቅኝ የመግዛት ህልም የለውም፡፡ የጣሊያን መንግሥት ዋነኛ ትኩረት በሸዋ አማራ አገዛዝ ሥር የሚማቅቁትን ሕዝቦች ለመታደግ ነው፡፡” ይል ነበር፤ የጣሊያን ፕሮፓጋንዳ፡፡  
ነገሩን የበለጠ ወለፈንዲ የሚያደርገው ከፋሺስት ወራራ በኋላ ለጥቀው የመጡት የ1960ዎች አጋማሽ ዘውጌ ተኮር ፖለቲካ ፓርቲዎች ከግር እስከ ራሳችው በዚሁ አውዳሚ ፕሮፓጋንዳ መጠመቃቸው ነው። በዚህ ረገድ ኦነግና ሕውኃት ይጠቀሳሉ፡፡ የእነዚህ ዘውጌ ተኮር ፖለቲካ ፓርቲዎች ታሪካዊ ጠላት አማራው እንደሆነ በማኒፌስቷቸው ላይ በግልጽ ሰፍሮ ይገኛል፡፡ አማራውን ጨቋኝ ሌሎች የሀገራችንን ሕዝቦች ደግሞ ተጨቋኝ በማድረግ የተዛባ ትንታኔ ላይ መሠረቱን የጣለው የጨቋኝ-ተጨቋኝ ተረክ፣ የፖለቲካ ፕሮግራማቸው የልብ ምት ሆኖ ላለፉት ሀምሳ ዓመታት አገልግሏል፡፡   
የኢትዮጵያ የታሪክ ገጽታን በቅጡ ከፈተሽነው ግን ለዘውግ አምላኪ ፖለቲካ ፓርቲዎች የተመቸ የዘር ልዩነትን ሲያስተናግድ አልኖረም። “Ethiopia: competing ethnic nationalisms and the quest for democracy, 1960-2000 በሚለው የዶክተር መረራ ጉዲና የዶክተሬት ሟሟያ ጽሑፍ ላይ ግሩም ቁምነገር ሰፍሯል።
“ጨቋኝ-ተጨቋኝ ትስስርን ጠለቅ ብለን ከተመለከትነው በእጅጉ የተሳከረ ነው። ለምሳሌ ሰፊው የኦሮሞ ህዝብ በጨቋኝ-ተጨቋኝ ወጥመድ ውስጥ ወድቆ ነበር። በምኒልክ ጦር ውስጥ የሸዋ-ኦሮሞዎች የአርሲ ኦሮሞዎችን ወይም የሀረር ኦሮሞዎችን በሀይል እንዲቀላቀሉ ከፍተኛ መስዋአትነት አድርገዋል። የሸዋ ኦሮሞዎች ለማዕከላዊ መንግሥት የቀረቡ ስለነበር በገዢነት ሚና ላይ ንቁ ተሳትፎ ሲያደርጉ ነበር። የምኒልክ የግዛት መስፋፋት ሥራ ያለ ሸዋ ኦሮሞ አርበኞችና ራሶች ፈጽሞ የማይታሰብ ነበር፤ታዲያ የቱ ተጨቋኝ የቱ ጨቋኝ ሊሆን ነው?”
የጨቋኝና ተጨቋኝ ተቃርኖ፣ የዘውጌ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ለፖለቲካ ትርፉ ሲባል የሚያራግቡት ፕሮፓጋንዳ ነው፡፡ በታሪክ ሒደቱ ውስጥ ዱካውን አስሰን ልናገኘው አንችልም፡፡ ምናልባትም የብሔር ጭቆና የሚለው ተረክ አለ ከተባለ፣ አጀንዳውን በሚያራምዱት ግለሰቦች ጭንቅላት ውስጥ ብቻ ነው። ታሪክን የኋሊት ተጉዘን መርምረን የምንደርስበት መደምደሚያ የፊውዳሉ የገዢ መደብ መለኪያው ከብሔር ይልቅ ኢኮኖሚያዊ እንደነበረ ነው፡፡ አንድ የአማራ ባላባት፣ ከአማራ ጭሰኛ ይልቅ ለኦሮሞ ወይም ለጉራጌ ባላባት ክብርና ሞገስ ይሰጣል፡፡ መለኪያው የሀብትና የሥልጣን ደረጃ እንጂ የዘውግ ማንነት አልነበረም፡፡
የ1987ቱ ሕገ መንግሥት ይህንን ነበራዊ ሁኔታ ሙሉ ለሙሉ በመካድ፣ በሀገራችን የታሪክ ሒደት ውስጥ ብሔራዊ ጭቆና እንደነበረ በማስመሰል፣ ብሔር ብሔረሰቦችን ከኢትዮጵያዊ ማንነት በላይ የሉአላዊ ሥልጣን ባለቤት አደረጋቸው፡፡ ይህም ህገ መንግሥታዊ ግርማ ሞገስን የተላበሰ የተዛባ ፍረጃ፣ ፍሬ አፍርቶ፣ በሀገሪቱ አራቱም ማእዘናት የተበተነውን ጨቋኝ ተብዬውን የአማራውን ዘውግ ጭዳ ያደርገው ጀመር፡፡  
ይህ አይነት በደልና ሰቆቃ በአንድ ወገን ላይ በተደጋጋሚ ጊዜ በተበራከተ ቁጥር ደግሞ የጥቃት ሰለባ ከሆነው ሕዝብ አብራክ የሚወለደው የዘውጌ ብሔረተኛው ክፍል የማይቀለበስ አጀንዳ ማግኘቱ የማይቀር ጉዳይ ይሆናል፡፡ የእንቅስቃሴው አራማጆች እንደ ቆስቋሽ ምክንያት ከሚወስዷቸው ነጥቦች መካከል የአማራው ዘውግ ላይ በሁሉም የሀገሪቱ ክፍል እየደረሰ ያለውን ዘርን ማዕከል ያደረገ ጥቃት ነው፡፡
ለዘውጌ ፖለቲካ ማበብ ትልቅ ሚና ከሚጫወቱ አብይ ምክንያቶች መካከል የተበዳይነት ወይም ወደ ዳር የመገፋት ኃይል መጠንከር ነው፡፡ የአማራ ብሔረተኞችም  ይህን የተብሰልሳይነት ስነ ልቦናን በመስበክ ነው አጀንዳቸው ቅቡልነት እንዲያገኝ ላይ ታች የሚሉት፡፡ “አማራው ላለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት በገዛ ሀገሩ የዳር ተመልካች እንዲሆን ተፈርዶበታል። ጥቃትን መመከት ተፈጥሯዊ አማራጭ ስለሆነ ማንነታችንን ታሳቢ አድርገን መሰባሰብ የሞት ሽረት ጉዳይ እንጂ የድሎት ጥያቄ አይደለም፡፡” ይላሉ፤ የፖለቲካ እንቅስቃሴው ፊት አውራሪዎች፡፡
በእርግጥም ኢህአዴግ መንበረ ሥልጣኑን ከተቆናጠጠ ወዲህ የፀራ-አማራ ተረክ ሥጋ ለብሶ ለዓይን የሚያስፈራ ወደል ሆኗል፡፡ በተረኩ ሴራ ቂም የቋጠሩ ኃይሎች ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ በአማራው ላይ  የጭካኔ በትራቸውን ከማሳረፍ አሰልሰው አያውቁም፡፡

የወልቃይት ጉዳይ
የ1987 ሕገ መንግሥትን ተከትሎ ለፍሬ የበቃው የፌደራላዊው ሥርዓት ሰለባ ካደረጋቸው ሕዝቦች መካከል በግንባር ቀደምትነት ሊጠቀስ የሚችለው የወልቃይት ሕዝብ ነው፡፡ የራስን ዕድል በራስ በማስተዳደር ውስጥ ወሳኝ ሚና የሚጫወቱ ነባራዊ ሁኔታዎች ወደ ጎን ተገፍተው፣ ለፍሬ የበቃው ፌደራላዊው ሥርዓት፣ ለወልቃይት ሕዝብ የምሥራች ይዞ አልመጣም፡፡ እትብቱ በተቀበረበት ሀገሩ ላይ ማንነቱን እንዲክድ ተፈርደቦታል፡፡ የወልቃይት ሕዝብ ጥቃት ለአማራ ብሔረተኛነት ማቆጥቆጥ ትልቁን ሚና ተጫውቷል ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ በዘውግ-ተኮር (ethinocenteric) ራስን በማደራጀት ሊመጣ የሚችለውን ተጨማሪ ጥቃት መከላከል በእጅ ላይ የቀረ ብቸኛ አማራጭ እንደሆነ የእንቅስቃሴው መሪዎች አጽንኦት ሰጥተው ይገልጻሉ፡፡  
የፌደራላዊው ሥርዓት በአንድ ክልል ውስጥ አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ዜጋን ስለሚፈጥር፣ ከክልላቸው ውጪ የሚኖሩ የአማራ ዘውግ ተወላጆች ዕጣ ፈንታ የሚወድቀው በአካባቢ ሹማምንቶች እጅ ላይ ነው። እነዚህን በሰፈራ፣ በስደት ወይም በግድ ወደ ሌላ ክልል የተካተቱን ወገኖች በሰላም የመኖር ዋስትና ሕገ መንግሥቱ ሊያረጋግጥላቸው አልቻለም፡፡ ሰማኸኝ ጋሹ ዘላስት ፓስት ኮልድ ዋር ሶሻሊስት ፌደሬሽን  በሚለው ድርሳኑ ላይ ከዚህ ነጥብ ጋር የሚቀራረብ ግሩም ነጥብ አስፍሯል፡-
Thus, the principle of the right to self-determination of nations and nationalities has resulted in the creation of new minority groups that have increasingly become second-class citizens in their own country and being subjected to internal displacement.  
ወልቃይቴው ፌደራላዊው ሥርዓት ባመጣበት ጣጣ፣ በተካለለበት ክልል ውስጥ ራሱን እንደ ሁለተኛ ደረጃ ዜጋ ለመቁጠር ተገዷል፡፡ ይህ በወልቃይት ሕዝብ ላይ እየደረሰ ያለው እንግልት ለአማራው ብሔረተኛ የተጠቂነትን ወይም የተበዳይነትን ስነ ልቦና ለመስበክ ትልቅ እገዛ ሆኖለታል፡፡

ማኅበራዊ ሚዲያ
ማኅበራዊ ሚዲያ የዜጎችን ስነ ልቦና በመቅረጹ ረገድ ጉልህ ድርሻ እየያዘ መምጣቱ  እንደሆነ ይታወቃል፡፡ አንድ ጦማሪ ከተቀመጠበት ወንበር ሳይነቃነቅ በሚሊዮኖች ላይ ተጽዕኖውን ለማሳረፍ አይቸገርም፡፡ ማኅበራዊ ሚዲያ በተለይ ወጣቱን አጀንዳ ተቀባይ ለማድረግ ምቹ መድረክ ሆኖ ማገልገሉ የአደባባይ ሀቅ ነው፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እንደውም የሀገራችን የፖለቲካ ምህዋር የሚሾረው በዚሁ ሚዲያ ሆኗል፡፡ የማኅበራዊ ሚዲያ አጀንዳ፣የሀገራችን መሪ አጀንዳ ከሆነ ሰነበተ፡፡ የቅርቡን የቄሮን እንቅስቃሴ  ለአብነት ያህል መጥቀስ ይቻላል፡፡
ገናና የማኅበራዊ ሚዲያ ጦማሪያን፣ የአማራውን ዘውግ ቀልብ ለመማረክ የኦንላይን መድረኩን በሚገባ እየተጠቀሙበት እንደሆነ ከተጽዕኗቸው መበርታት መገንዘብ እንችላለን፡፡ የእንቅስቃሴው ቀንደኛ መሪዎች ዋንኛ የግንኙነት መረብ ማኅበራዊ ሚዲያ ነው፡፡ ሀገር ውስጥ ያሉትን ተከታዮቻቸውን ስብሰባ የሚጠሩበት ወይም በግልጽ የሚወያዩበት አማራጭ ሳይኖራቸው፣ በአማራው ሕዝብ ላይ የሚደርሰውን በደል በምስልና በድምጽ የተቀነባበረ መረጃ በማድረስ፣ የብዙዎችን ቀልብ ለማቸነፍ አልተቸገሩም፡፡  

ማጠቃሊያ
የአማራው ዘውግ፣ ኢትዮጵያዊ አርበኝነትን እንደ ካስማ በልቡ ተሸክሞ የኖረ ሕዝብ ነው፡፡ ከበቀለበት ዘውግ ይልቅ ለእናት ሀገሩ ደምና አጥንቱን ከስክሶ፣ ይቺን የመሰለች ታሪካዊት ሀገር ታፍራና ተከብራ እንድትኖር ግንባር ቀደም ሚና ሲጫወት ኖሯል። ይህንን ታላቅ ሕዝብ ወደ አንድ ጠባብ የዘውግ ማንነት እንዲሰባሰብ መግፋት፣ በሀገር አንድነት ላይ የሚኖረው አሉታዊ ተፅእኖ አደገኛ ነው፡፡ ዛሬ ጠንካራ አማራ ማኅበረሰብን ለመፍጠር ትልቅ ድጋፍ የለገሰው ወገን፣ ነገ ከነገ ወዲያ በበቀለበት ጠባብ ዘውግ ዙሪያ መሻኮቱ አይቀርም፡፡ ጠንካራ አማራነት ውሎ አድሮ የጠነከረ ጎጃሜን፣ወሎዬን፣ ሸዋንና ጎንደሬን  ለዓይነ ሥጋ ያበቃል፡፡ ይህም በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ቀዳሚ ሆኖ ከመሰለፍ ይልቅ በአካባቢ ወይም በጥቃቅን ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ተቀንብቦ መቅረትን ሊያስከትል ይችላል፡፡
በአጠቃላይ የስቃይ በትርን ጫንቃው አልችል ያለ ሕዝብ የሚኖረው ጭላንጭል ዕድል ወደ ራሱ ወይም ወደ ውስጥ በመሰበሰብ ጥቃትን የመመከት ስልትን መቀየሰ ነው፡፡ ይህ ግን ዘላቂ መፍትሄ አይሆንም፡፡ እሳት የማጥፋት ሚና ብቻ ነው የሚኖረው፡፡ በሀገራዊ አንድነት ጥላ ሥር ከሌሎች የሀገራችን ሕዝቦች ጋር በመተባበር ከሚያንዣብበው አስፈሪ መጻኢ ዕድል በሚታደግ ተጨባጭ የፖለቲካ አቅጣጫ ላይ ንቁ ተሳትፎ ማድረግ ከተሳነን ከአዙሪቱ መላቀቅ አንችልም።

No comments:

Post a Comment